Thursday, February 14, 2013

ቀባሪ ያጣው የወያኔ/ኢህአዴግ የአገዛዝ ስረአትና ባለቤት የሌላት ኢትዮጵያ

እንደ ወያኔ/ኢህአዴግዊ ሀገርንና ትውልድን የሚያጠፋ እኩይ አመለካከትና ምግባር ይዞ ተነስቶና ተሳክቶለትም የሚገዛ ከኢትዮጵያ ውጭ በአለም ላይ ያለ ሀገርም ሆነ የሚገዛ ህዝብ የለም። እንደ ወያኔ/ኢህአዴግ የገዛ ወገኑንና ሀገሩን በጠላትነት ፈርጆ፣ ታጥቆና ተደራጅቶ የሚወጋና የሚያፈራርስ የለም። እንደ ወያኔ/ኢህአዴግዊ አገዛዝም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊንን የማጥፋቱንና የመበታተኑን ምግባር እንዲያቆም እሽሩሩ የተባለና እየተለመነ ያለ የለም።…..
በልመና ቢሆን…..
ፍትህ – እኩልነት
በልመና ቢሆን…
ነጻነት – አንድነት
በልመና ቢሆን….
ሰላምና ሕይወት፤
እመጣ ነበረ- አንች ካለሽበት
ትመጭልኝ ነበር – እኔ ካለሁበት
ዓለም ይሆን ነበር፣ የሁላችንም ቤት።
እንደ ደርግ ያለ አምባገነን መንግስት ሀገሩን በክህደትና በጥላቻ ለተሞሉ፤ እንደ ሻአቢያዊንና እንደ ወያኔያዊያን ላሉ ሀገሩን አሳልፎ የሰጠ የለም። እንደ ወያኔ/ኢህአዴግ ያሉ ተቃዋሚዎች ልፍስፍስ፣ ወኔ ቢስ፣ እርስ-በርስ የሚናቆሩና ከትላንቱ የማይማሩ፣ ሁሌም የጠላት መሳሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ”ቦለቲከኞች” ማግኘት ይከብዳል።
አንድ ጀርመናዊ የጥንት ፈላስፋ ”መግደልም ሆነ መገደል በፍጹም አልፈልግም፤ ግን ክብሬ ከሚዋረድ ከሁለቱ አንዱን እመርጣለሁ።” ማለቱ ይነገራል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን ሳንታገለም፣ ሳንኖርም፣ የቁም ሞትንና የውርደት ህይወትን ”መኖር” ብለነው፤ ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር በባንዳ ልጆች፣ የልጅ ልጆቻቸውና በሆድ-አደር ሎሌዎች ስትፈራርስና አንጡራ ሀብቷ የባዕዳንና የወያኔዎች መቀለጃ ሲሆን እያየን አመታት አሳለፍን። ግፋ ቢል እነሱ ስራቸውን ሲሰሩ አኛ አናወራላቸዋለን። እጅግ በጣም ጥቂት በጣት የሚቆጠሩት እውነተኛ ሀገራዊ ትግል ቢጀምሩም፤ በግፈኛ ወያኔውዎች የሚደርስባቸው ግድያና እስራት አንሷቸው፤ አኛ የተለያየ ስም እንሰጣቸዋለን።
በዚህ በያዝነው ዘመን፣ ሰው ”ሰው” በመሆኑ ብቻ ተከባብሮና ተሳስቦ፤ ድንበር እያፈረሰ በአብሮነት መኖርና መበልጸግ በተቻለበት አለም፤ በኢትዮጵያ ግን ለእውነትኛ ሀገራዊ ልዕልና፣ ለህዝቦቿ አንድነተና ህልውና የሚቆም መጥፋቱ ሲታሰብ፤ የምናሳዝንና የሚታዘንልም ዜጎች ብቻ ሳንሆን፤ በእርግጥም ጤንነታችንም የሚያጠያይቅ ነው። ለዚህም ነው አቶ ገሪማ መታፈሪያ የሚከተለውን ስንኝ የቋጠሩት:: …
”… ሁሉ በሽተኛ፣ ሁሉ ራሴን ባይ
ባሀገሬ ደህና ሰው ላይገኝ ነወይ?
ባሀገሬ ጤነኛ ላይገኝ ነወይ?…” ።
በአጠቃላይ በስብዕናችን፣ በመፈሳዊነታችን፣ በማንነታችን፣ በኢትዮጵያዊነታችን … ወርደን … ወርደን… ወርደን…
- በአለም የመጨረሻዋ ደህ፣ተመጽዋችና ስደተኛ ህዝቦች መሆናችን አልበቃ ብሎ፤ አንድ ቁጥር ዘረኛና አምባገነን ስርአት የምናስተናግድና ‘’ኢትዮጵያዊ አይደለንም እያሉን’’ የምንገዛ እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን።
- ገዥዎቹ ወያኔዎችና ሆድ-አደር ሎሌዎቻቸው በአለም ላይ አንድ ቁጥር የደሀ-ደሀ የሆነች ሀገር እየገዙ፤ ባለጸጋ ሀገሮች እንኳ’ ሊያልሙት የማይችሉትን የተደላቀቀና የተፈላሰሰ ግን የአውሬነት ኑሮ የሚኖሩባት ሀገር ኢትዮጵያችን ነች።
- ፊደል ቆጥረናልና ተምረናል የሚሉት የሀገሪቱ ዜጎች፤ ያስተማራቸውን ህዝብ ከድህነተና ከድንቁርና አውጥቶ፣ ፍትህና እኩልነት ያለበት ሀገር ለመገንባት በመታገል ፋንታ፤ ከእነ’ሱ በእውቀትም ሆነ በስብዕና ለሚያንሱ የወያኔ ቡድኖች ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን፣ ወገናቸውንና ሀገራቸውን ለሆዳቸው፣ በሆዳቸው የሚሸጡ ፍጡራን እንደ አሸን የሚፈላባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች።
- ዜጋው መጠለያ ጎጆ የሚቀልስበት ቦታና ጥማድ በሬዎቹን የሚያውልበት ሽራፊ መሬት ተነፍጎት፤ የኢትዮጵያን ውድቀትና ጥፋት እንደ ማለዳ ጸሀይ ለሚናፍቁ፤ ግን እየተለመኑ ሀገር እየተቆረሰ የሚታደልባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች።
- በተለይም ወጣቱ ትውልድ በአገዛዙና በሀገሪቱ ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ፤ የሚበጀውን ለራሱና ለወገኑ ከመታገል ይልቅ፤ ባዕዳን’ ተስፋ በማድረግ፤ ለባህርና ለውቅያኖስ አሳ ነባሪ፣ እንዲሁም ለበርሀ አሸዋ ‘ራሱን አሳልፎ በመስጠት ትውልድ እየጠፋባት ያለች ሀገር ኢትዮጵያ ነች። በህይወት የተረፈም ለግርድናና ለሽርሙጥና ሲዳረግ፤ በሞቱት ስደተኛ ወገኖቹ የሚቀና ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው።
- የህክምና ባለሙያዎች፤ በማንኛውም መንገድ ይሁን የሰውን ልጅ ህይወት የመርዳትና የማትረፍ አላማ አድርገው በደሀው የገበሬ ገንዘብ እንዳልተማሩና ቃለ-መሀላ እንዳልፈጸሙ ሁሉ፤ ወገናቸው ህክምና ፍለጋ አግዳሚ ወምበር ላይ ተጋድሞ እያቃሰተ እያዩት፤ ነገር ግን የሀይል መስጫ ምግብ (ግልኮስ) መግዣ ለግዜው ሳንቲም ስሌለው ብቻ ህይወቱ እንድታልፍ ”ፍርድ’ የሚሰጣባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች።
- የሀይማኖት አባቶች እጅግ በሚዘገንና በማይታመን መልኩ በዘረኝነትና በአፍቅሮ ንዋይ ታውረው፤ ለገዥዎች ሎሌነት በማደር፤ እምነት የረከሰባትና የተናቀባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች።
- የሀገሪቱ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፤ ንፋስ ወደ ነፈሰበት እየነፈሱ፣ የገዥዎች አፍና እጅ በመሆን፤ ክቡሩ የህሊና ሙያ ለከርስና ለጥቅማጥቅም የሚቸበቸብባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች።
- ወያኔዎች የዘሩት የዘረኝነት ዘር አፍርቶ፤ በአሁኑ ወቅት የአንድ ቤት-ቤተሰብ አባላት እንኳ’ የማይተማመኑበትና፤ ወንደሙ፣ ወንድሙን ለጥቅም አሳልፎ የሚሰጥበት ሀገር ኢትዮጵያችን ነች።
- ኢትዮጵያ… ግፈኞች፣ ወንጀልኞች፣ አምባገነኖች፣ ከሀዲዎች፣ ሆድ-አደሮች፣ ውሸታሞች፣ ሌቦች፣ ባንዳዎች፣ ሙሰኞች፣ ጠባብ መንደርተኞችና ህሊና ቢሶች በኩራት ደረታቸውን ነፍተው የሚጎሩሩባትና እንደ ሜዳ አህያ የሚፏሉሉባት፤ በተቃራኒው ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለህሊናቸው፣ ለሀገራቸው ልዕልናና ለህዝባቸው ፍትህና እኩልነት የሚታገሉና የሚደክሙ አንገታቸውን ደፍተውና አቀርቅረው የሚሄዱባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች።
…ግን ምነዋ ኢትዬጵያ…?
እንደ ይሁዳ ከዱ ልጆችሽ ሸፈጡ
እንደ ኤሳው ሆኑ ቡክርናቸውን ሸጡ
በመታመን ፋንታ ኑፋቄን መረጡ።
እንደ ባህር አሸዋ – እንደ ሰማይ ከዋከብት
ምነዋ ኢትዬጵያ… በዛብሽ ጠላት?…

Posted By.Dawit Demelash




No comments:

Post a Comment