የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአሜሪካ በሚገኙ አባቶች ሲኖዶስ ላይም ሊዘምት ነው
ሐራ ዘተዋሕዶ
- አራተኛውን ፓትርያሪክ ጨምሮ ሦስት አባቶች ተተኩሮባቸዋል
- ጠ/ቤ/ክህነቱ ለዶክመንተሪው ስርጭት ከብር መቶ ሺሕ ብር በላይ መክፈሉ ተነግሯል
‹‹የነውጥን ጎዳና የመረጡ የሩቅ አገር ናፋቂዎች›› በሚል ርእስ መቀናበሩ የተነገረለት ይኸው ዶኩመንተሪ÷ በዋናነት፣ በአራተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ እና አቡነ መቃርዮስ ላይ የሚያተኩር ነው ተብሏል፡፡
ዝግጅቱ ለአንድ ሰዓት ከ30 ደቂቃ የሚዘልቅ ሲሆን በሁለት ተከታታይ ክፍል እንደሚቀርብ ተገልጧል፡፡ የዝግጅቱ ዓላማ/ፋይዳ÷ በውጭ በስደት የሚገኙ አባቶችን ‹‹የኋላ ማንነት እና የወቅቱን አቋም ማጋለጥ››፣ በዚህም ቀጣይ አካሄዶቻቸውን ‹‹ተቀባይነት ማሳጣት›› እንደኾነ ተመልክቷል፡፡
አራተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ÷ ከምንኲስና እስከ ፕትርክና የነበራቸው ጉዞ፣ ለፕትርክና የበቁበት መንገድ እና ከቀድሞው ሥርዐተ መንግሥት ጋራ የነበራቸው ግንኙነት በዝግጅቱ የተካተተ ሲሆን በተለይም በጎንደር ሥርዐቱ በዜጎች ላይ ፈጽሞታል በሚለው በደል ነበራቸው የሚለውን ተሳትፎ በማተት ይወነጅላቸዋል፡፡ ቅዱስነታቸው ከሥርዐቱ ለውጥ በኋላ ከፕትርክና ‹‹በፈቃዳቸው›› ስለወረዱበት ኹኔታ፣ የወቅቱ የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ጽፈውታል ስለሚባለው ደብዳቤ፣ ከአገር ስለወጡበትና በኬንያ የነበራቸውም ቆይታ የዶኩመንተሪ ዝግጅቱ አካል ነው ተብሏል፡፡
ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን በተመለከተ በዶኩመንተሪው ከብፁዕነታቸው ማንነት በመነሣት የአምስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሢመት ሲከናወን በአገር ውስጥ እንደነበሩና ሢመተ ፕትርክናውን ስለመቀበላቸው በማተት ከአገር ከወጡ በኋላ የያዙትን አቋም ይነቅፋል፡፡ በተለይም ደግሞ ‹‹እስላሙ ወገናችን ክርስቲያኑን በመደገፍ፣ ክርስቲያኑ ወገናችን እስላሙን በመደገፍ ይነሣ›› በማለት ባለፈው ዓመት ባስተላለፉት ጥሪና ባወጡት መግለጫ ሳቢያ በአሸባሪነት ይከሳቸዋል ተብሏል፡፡
በሰሜን አሜሪካ በስደት የሚገኙ አባቶች ባቋቋሙት ሲኖዶስ የአፍሪካና የአውሮፓ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የኾኑት አቡነ መቃርዮስ እንደ ግንቦት ሰባት እና አርበኞች ግንባር ካሉት፣ መንግሥት በአሸባሪነት ከፈረጃቸው የተቃውሞ ድርጅቶች ጋራ አብረው እንደሚሠሩ በመጥቀስ በአሸባሪነት እንደሚወነጅላቸው ተመልክቷል፡፡ ለዚህም በአስረጅነት የቀረበው የተጠቀሱት አባት በኤርትራ ያደረጉት ጉብኝት መኾኑ ተጠቅሷል፡፡
በዶኩመንተሪ ዝግጅቱ÷ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃንና ሁለት የታሪክ መምህራንን ጨምሮ ከኢትዮጵያው ሲኖዶስ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት በቃል አስረጅነት እንደተካተቱበት የተዘገበ ሲኾን ለቃለ ምልልስ የትብብር ጥያቄ ቀርቦላቸው ዝግጅቱን በመሠረቱ የተቃወሙና ፈቃዳቸውን የነፈጉ አባቶችም እንዳሉ ተዘግቧል፡፡ ከሁሉም በላይ ምናልባትም አስገራሚና አሳዛኝ ሊባል የሚችለው ነገር ግን፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዶኩመንተሪው እንዲዘጋጅ የወሰደው ተነሣሽነትና ለሚተላለፍበት የአየር ሰዓት እንደፈጸመው የሚነገረው ከመቶ ሺሕ ብር በላይ የኾነ ክፍያ ነው፡፡
ድርጅቱ (ኤሪቴድ)÷ በነገው ዕለት፣ ጥር 28 ቀን 2005 ዓ.ም ምሽት ‹‹ቦኮ ሓራም በኢትዮጵያ/ ጅሃዳዊ ሓራካት›› በሚል ርእስ ‹‹በኢትዮጵያ እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት›› ደረስኹበት ያለውን ዝግጅት እንደሚያቀርብ እያስተዋወቀ መኾኑ ይታወቃል፡፡
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment