Thursday, February 28, 2013

የሳጅን ዘመድኩን ዛቻ እና ትርጉሙ

FEB.28.2013
ለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፈለ ከተማዎች የወያኔ መንግስት ፓሊሶችና ደህንነቶች በሙስሊሙ ወገኖቻችን መኖሪያ ቤቶች በመዘዋወር ዝርፊያ የተቀላቀለበት አሸባሪ ብርበራና ፍተሻ ሲያካሄዱ ሰንብተዋል። ይህ ብርበራ በአይነቱ ፍጹም ከሆነ የወሮባላ ተግባር የተለየ እንዳልሆነ የደረሰባቸው፣ ያዩና የሰሙ ሁሉ የሚመሰክሩት ነው።
የፍርድ ቤት ትእዛዝ ለይስሙላ እንኳን ያልያዙ ጭንብል ያጠለቁ ፓሊሶችና ደህነነቶች ጨለማን ተገን በማድረግ በር እየበረገዱ በመግባት ቅዱሳን መጸሃፍትን፣ ሞባይልን፣ ቴሌፎኖን እና ወርቅ በግፍ መዘረፋቸውን ሰለባዎቹ አረጋግጠዋል። ይህ በእነዚህ ንጹሃን ሙስሊም ወገኖች ላይ ከተፈጸመው ድብደባ፣ ማስፈራሪያና ማስደንገጫ ተጨማሪ መሆኑ ነው።
የእነዚህን አሳዛኝ ግፈኛ ተግባር የሰማው የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ዜናውን በየካቲት 14 ቀን 2005 አ.ም ምሽት ዘግቦ ነበር። በዚህ ዘገባ ላይ የቪ.ኦ.ኤው ጋዜጠኛ የሰለባዎቹን ምስክርነትና አስተያየት ብቻ ማቅረብ ተገቢ ያልመሰለው ፕሮፌሽናሉ ጋዜጠኛ፣ ሚዛናዊ ዘገባ ለማቅረብ ድርጊቱ ተፈጸመባቸው ወደተባሉት ክፍለ ከተማዎች የፓሊስ አዛዦች መደወል ነበረበት። ይኼኔ ነበር ጋዜጠኛው ሳጅን ዘመድኩንን ያገኘው። ይህን የመንግስት ወንጀል እንዲያስተባብሉ እድል የተሰጣቸው ሳጅን ዘመድኩን የሰጡት መልስ ሰዋዊ ሳይሆን አውሬያአዊ ነው ማለት ይቻላል።
የተሰራውን ግፍ መዘገቡ ያናደዳቸው የፖሊስ አዛዦች ጭራሹኑ ጋዜጠኛውን ራሱን አሁን መጥቼ አስርሃለሁ የሚል መልስ ነበር የሰጡት። እብሪተኛው ሳጅን ጋዜጠኛው እንኳን ዋሽንግተን መንግስተ ሰማያትም ገብቶ እንደማያመልጠው ካዛቱ በኋላ ቃለ ምልልሱ አለቀ።
ይህን ቃለ ምልልስና የሳጅን ዘመድኩን ዛቻ ስንሰማ ቅጽበታዊ ምላሻችን ሳቅና መገረም ሊሆን ይችላል። ከዚህ የደንቆሮ ሃሳብ ከሚመስል አስቂኝና አስገራሚ አነጋገር በስተጀርባ ግን በእጅጉ የሚያሳዝን፣ የሚያስለቅስና የሚያስቆጭ ትርጉም አለው። የሳጅን ዘመድኩን ጥያቄ አመላለስ የልዩ አጋጣሚ ጉዳይ (Isolated Event) አይደለም። እንደዚያ ከመሰለን ክፉኛ ተሳስተናል። በሳጅን አንደበት የሰማነው አውሬ ወይም የህወሃት ድምጽ ህዝባችን በእየለቱ ቁም ስቅሉን የሚያሳየውን የወያኔ የየእለቱን ዘረኛ ቋንቋ እና ተግባር ነው። ሳጅን ዘመድኩን የተናገረው የሰለጠነበትንና ወያኔ የወሰነውን ነው በእሱ ልሳን የሚናገረው።
ወያኔዎች የፈለገንን አድርገን አዋርደን እንገዛችኋለን፤ ምን አባታችሁ ትሆናላችሁ ነው የሚሉን በወያኔኛ ቋንቋ። ሳጅን ዘመድኩን እንደምንገምተው ደንቆሮ አይደለም። ወያኔ ውስጥ ያደገ ወያኔኛ የተማረና የሰለጠነ፣ ሁሉንም ጣቢያዎች ከሚያዙት ሰዎች አንዱ ነው። ትእዛዝ ፈጻሚ ወያኔ ነው። ህዝብ ደሞዝ የሚከፍለው የህዝብ ተቀጣሪ ነኝ ብሎ አያምንም። እንደሁሉም ወያኔዎች እየዘረፈ የሚኖር ሽፍታ ነው። ህግና ህገ-መንግስት ለጌጥ የተቀመጠ መሆኑን ወያኔዎች ሁሉ ያውቃሉ። ተናግረውታልም።
በሳጅን ዘመድኩን አራዊታዊ አነጋገር ስቀን ከሆነ የሳቅነው በራሳችንና በህዝባችን ሰቆቃ ነው። በራሳችን ውርደት ለመሳለቅ አይተናነስም።ሀገራችን በእንደ እነ ሳጅን ዘመድኩን ያሉ ሰዎች ነው የምትመራው። ትልቅ ውርደት ላይ ነን። ሀገራችን ከውረደት፣ ህዝባችንን ከሰቆቃ የማዳን ግዜው አሁን ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፡- ምርጫችን ሁለት ነው። ወይ “ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል እያልን የቁም ሞት ኑሮአችንን መኖር” አሊያም ወያኔን አስገድደንም ሆነ አስወግደን የሚገባንን የኩሩ ህዝብና ሀገር ስብእናችንን ማስመለስ እና ሀገርን ከማዳን ከሞራላዊ ግዴታ ተጠያቂነት ነጻ የመሆን።
እንዳንሳሳት! የሳጅን ዘመድኩን አራዊታዊና እብሪታዊ ቋንቋ ወያኔያው የእለት ተእለት ዘይቤ ነው። ስለዚህ ጀንበር ቁልቁል ሳትጠልቅብን ወያኔን አስገድዶ ለመጣል ከሚንቀሳቀሰው ህዝባዊ ሃይል ጋር በመሆን የመታገያ ጊዜው አሁን ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment