Wednesday, February 27, 2013

የሕወሐት ፍጥጫ ቀጥሏል « አሁን ያለው ሕወሐት ቆዳ ነው » እነ ስብሃት « የሕወሐት ወራሾች እኛ ነን » እነ አባይና አዜብ (ከኢየሩሳሌም አርአያ)

ሁለት ቦታ የተከፈለው የሕወሐት አመራር ልዩነቱን በማስፋት እየተወዛገበ መሆኑን ከመቀሌ ታማኝ ምንጮች ገለፁ። ስብሃት እና አዜብ የሚመሩት ሁለቱ ቡድን አነጋጋሪ አቋም ይዞ መውጣቱን ምንጮቹ ጠቁመዋል። በስብሃት ነጋ የሚመራው ቡድን ባስቀመጠው አቋም « መለስ ሕወሐትን ገድሎ ነው የሔደው! አሁን ያለው ሕወሐት ቆዳ ነው። ጥያቄው ግልፅ ነው፤ ሕወሐት መቀጠል አለበት.. ወይስ የለበትም?» ሲሉ በድርጅቱ ቀጣይ ሕልውና ላይ ጥያቄ አሳርፈዋል። ከዚህ በተቃራኒ የቆመውና አባይ ወልዱ፣ አዜብና ከጀርባ በረከት ስምኦን ያሉበት ቡድን በበኩሉ « የሕወሐት ወራሾች እኛ ነን፤» ሲል ለነስብሃት ምላሽ መስጠቱ ታውቋል። በተጨማሪ በሁለቱም ቡድኖች በልዩነት ነጥብ ተደርጎ የተወሰደው በ1993ዓ.ም ከፓርቲው የተባረሩት አመራሮች « ይመለሱ» ፣ « አይመለሱም» የሚለው እንደሚገኝበት ተጠቁሟል። የሁለቱም ጐራ ፖለቲካዊ ግብ አንዱ ሌላኛውን ገፍትሮ ከሜዳው ማስወጣትና ፓርቲውን ብሎም አገሪቱን በፈላጭ ቆራጭነት ለመቆጣጠር ያለመ እንደሆነ አንድ የፓርቲው ቅርብ ሰው ጠቁመዋል።
በፓርቲው በተለኮሰው ስር የሰደደ ፖለቲካዊ ፍጥጫ ካድሬው ለሁለት ተከፍሎ ሲነታረክ መሰንበቱን ምንጮች ጠቁመዋል። በፓርቲው አባላት « አደገኛ» የተባለውን ይህን ፍጥጫ መሰረት በማድረግ በቴውድሮስ አድሃኖምና ብርሃነ ገ/ክርስቶስ የሚመራ ቡድን ራሱን « የአስታራቂ ሽማግሌዎች ቡድን» በሚል ሰይሞ ባለፉት ቀናት ሲነቀሳቀስ መቆየቱን ገልፀዋል። ሆኖም ሁለቱን ጎራዎች አቀራርቦ ለማነጋገርና ለማስማማት የተጀመረው ጥረት በሁለቱም በኩል በሚታየው አክራሪ አቋም ምክንያት ተስፋ ሰጪ ሁኔታ እንደማይታይ ምንጮቹ አስታውቀዋል። አሁንም ድርድሩ መቀጠሉን ምንጮቹ አልሸሸጉም።
የሕወሐት ሕልውና አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት በአሁኑ ወቅት በሌላ ጐራ የተነሱ ወጣት የፓርቲው ካድሬዎች ባነሱት ጥያቄ ፥ ሁሉም አንጋፋ አመራሮች ከድርጅቱ እንዲለቁ ጥያቄ ማቅረባቸውንና ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆኑ ግን ሕወሐት ሊፈርስ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ጭምር መስጠታቸውን ምንጮቹ አያይዘው ገልፀዋል።
በተያያዘም « ጉባኤ ይጠራ» በሚል በካድሬዎች የቀረበውን ጥሪ እነ አባይ ወልዱና አዜብ ያሉበት ቡድን ውድቅ እንዳደረገው ታውቋል። አባይና አዜብ የሚመሩት እንዲሁም ትርፉ ኪዳነማሪያም፣ ሃድሽ ዘነበ፣ አለም ገ/ዋህድ፣ በየነ ምክሩ፣ ተክለወይኒ አሰፋና ሳሞራ የኑስ የተካተቱበት ቡድን በጉባኤው አሸናፊ ሆነው እንደማይወጡ ከወዲሁ በማመናቸውና በነስብሃት በኩል ከፍተኛ ሃይል እንደተደራጀባቸው ጠንቅቀው ስለተረዱ ነው ሲሉ የጠቆሙት ምንጮቹ አክለውም ሳሞራ በመከላከያ እጣ ፈንታቸው ተመሳሳይ መሆኑን በማመናቸው ከነአዜብ ጋር ተሰልፈው እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የበላይነትን እየያዘ ነው የሚባለውና በስብሃት የተደራጀው እንዲሁም በደብረፂዮን የሚመራው ቡድን አብዛኛውን የማ/ኮሚቴ አመራር በዙሪያው ያሰባሰበ ሲሆን ከነዚህም፥ አዲስአለም ባሌማ፣ አርከበ እቁባይ፣ ቅዱሳን ነጋ፣ ፈትለወርቅ፣ ፀጋዬ በርሄ፣ አባዲ ዘሙ፣ ሃ/ኪሮስ ገሰሰ፣ ተ/ብርሃን…በዋንኛነት እንደሚገኙበት ምንጮቹ አመልክተዋል። የሽማግሌው ቡድን ስብስባ እንደቀጠለ ተጠቁሞዋል።

    Posted By.Dawit Demelash



No comments:

Post a Comment