ሕዝቡ በምርጫ እንዳይሳተፍ ጥሪ ቀረበ
ጥር ፳፬ (ሀያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአዴግ ሊያካሂደው ባሰበው የአካባቢ ምርጫ እንዳይሳተፍ 39ኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሪ አቀረቡ።
ፓርቲዎቹ ህዝባዊ ጥሪውን ያቀረቡት ”ኢህአዴግ ስለ አካባቢ ምርጫ የሰጠው መግለጫ የጥያቄዎቻችንን ትክክለኛነትና አግላይ አቋሙን ያረጋገጠበት ነው” በሚል ርዕስ ባወጡት መግለጫ ነው።
የ ኢህአዴግ ምክር ቤት ጸሀፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን ፓርቲዎቹ በምርጫ ላለመሳተፍ መወሰናቸውን አስመልክቶ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ፦<<እነሱ ተሳተፉ አልተሳተፉ የሚጨምሩትም፤የሚቀንሱትም ነገር የለም>> ማለታቸው ይታወሳል።
የ አቶ ሬድዋን መግለጫ ኢህአዴግ ዛሬም በ አገራዊና ህዝባዊ ጉዳዮች ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች በሙሉ ወሳኝም፣ ባለመፍትሔም እኔ ብቻ ነኝ ከሚል የ እብሪት ስሜት አለመላቀቁንና ሀላፊነት በጎደለው ጭፍን ጥላቻ እየተነዳ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል።
ባሻገር አህአዴግ በዋና ጸሀፊው አማካይነት የሰጠው መግለጫ በውሸት የታጀለ እና እርስ በርሱ የሚጣረስ እንደሆነ ፓርቲዎቹ በርካታ አብነቶችን በመጥቀስ አመላክተዋል።
አክለውም “ይህ አካሄድ ለማንም የማይጠቅም ከመሆኑም በላይ ብዙ ርቀት ሊያስኬደው እንደማይችል በድጋሚ ሊገለጽ ብቻ ሳይሆን በህዝባዊ ሀይል ሊገታ የሚገባው መሆኑን እንረዳለን” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ደጋግመን እንደገለጽነው ጥያቄዎቻችን ቀላሎች ናቸው ያሉት ፓርቲዎቹ እነሱም፦መንግስትና ኢህአዴግ ይለያዩ፣የመገናኛ ብዙሀን ፍትሀዊ አጠቃቀም ይኑር!፣የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ይከበር!፣ምርጫ ቦርድ ከገዥው ፓርቲ ተጽዕኖ ተላቅቆ በነፃነት ይደራጅ!የህግ የበላይነት ይረጋገጥ!፣በገዥው ፓርቲ አማካይነት ለ አፈና የወጡ ህጎች ይሻሩ! በድምሩ የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው የህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ይረጋገጥ ዘንድ የምርጫ ሜዳው ይስተካከል የሚሉ ናቸው ሲሉም መሰረታዊ ጥያቄዎቻቸውን አስፍረዋል።
ነገር ግን ከ ኢህአዴግ መግለጫ ለመረዳት የቻልነው ገዥው ፓርቲ ባለፉት 21 ዓመታት በሄደበት የማናለብኝነትና የሀይል መንገድ ለመቀጠል መወሰኑን እና ችግሮችን ለማስተካከል ፈቃደኛ አለመሆኑን ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፤በመሆኑም በምርጫው መሳተፍ የወንጀል አጃቢ ከመሆንና ለገዥው ፓርቲ ይሁኝታ ከመስጠት በዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ተገንዝበናል ብለዋል።
መላው የ አገራችን ህዝብም የምርጫው አካል በመሆን ኢዲሞክራሲያዊና ኢህገ-መንግስታዊ ለሆነ አካሄድ ይሁኝታ እንዳይሰጥ ጥሪ እናቀርባለን በማለትም ህዝቡ በምርጫው እንዳይሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
<<ፓርቲዎቹ መግለጫቸውን ሲቋጩም፦በተባበረና በተቀናጀ ህዝባዊና ሰላማዊ ትግል ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት፤እንዲሁም ከድርጅታችን ይልቅ ለ አገራዊ የህዝብ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት በትብብር ለመሥራት ቃላችንን እናድሳለን>>ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢህአዴግ ለምርጫ ቀስቃሾች የሚያወጣው ገንዘብ አስደንጋጭ ሆኗል
ኢህአዴግ በመጪው ሚያዚያ ወር ለሚካሄደው የአዲስ አበባ፣ የድሬዳዋ ከተሞች እና የክልል ምክር ቤቶች እና የወረዳዎች ምርጫ በርካታ ሰዎች የምርጫ ካርድ እንዲያወጡ ቤት ለቤት ለሚቀሰቅሱለት ካድሬዎቹ የቀን ውሎ አበል እና የስብሰባዎችና ድግሶች በሚሊዮኖች የመንግሥት ገንዘብ እያወጣ መሆኑን ምንጮች አስታወቁ፡፡
በርካታ ሰዎች ካርድ እንዲያወጡ ቤት ለቤት እንዲቀሰቅሱ መልምሎ የላካቸው በዝቅተኛ ገቢ ላይ የሚገኙ እናቶችን፣ ሴቶችን እና ወጣቶችን ከሴቶች ሊግ፣ ከወጣቶች ሊጎች እና ፎረምና ወጣት ማህበራት እና ዝቅተኛ የየአካባቢው ካድሬዎቹን መልምሎ ሲሆን በቀን ከሃምሳ ብር እስከ 250 እንደ ቀኑ ውጤታቸውና ደረጃቸው እየከፈለ ነው ፡፡
ለአንዳንዶቹም በድርጅቱ ደብዳቤ ለሚመለከታቸው የሥራ መስኮች- የአንበሳ አቡቶቡስ ቴኬት ቆራጭነት፣ በየሴክተርና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በተላላኪነት፣ በአትክልተኝነት፣ በጥበቃ ሠራተኝነት ለመቅጠር ቃል በመግባትና የድጋፍ ደብዳቤ በመስጠት እና ነቃ ያሉ ወጣቶችን ደግሞ ተደራጅተው በሚፈልጉት የሥራ መስክ እንዲሰማሩ የገንዘብ ብድርና የመሥሪያ ቦታ ለማመቻቸት ቃል እንደገባላቸው ታውቋል፡፡ ያስቀመጠው የምርጫ ኮታ ባለመሙላቱም በልዩ ልዩ ምክንያት ላልተመዘገቡ ሰዎች በሚል ምርጫ ቦርድ ለተወሰኑ ተጨማሪ ቀናት ምዝገባውን እንዲቀጥል በውስጥ ደብዳቤ አዞአል ፡፡
የኢህአዴግ ካድሬዎችና በየማህበራቱ ያደራጃቸው ወጣቶች ቤት ለቤት በሚያደርጉት የማስመዝገብ ዘመቻ የቤቱ አባወራ እና እማወራ በማያውቁበት ሁኔታ በቤት ውስጥ ለእንግድነት የመጡ ሰዎችን፣ የቤት ውስጥ ሠራተኞችን ሳይቀር ጊዜያዊ የቀበሌ መታወቂያ ወረቀት በቀበሌዎችና ወረዳዎች በማሰጠት ድርጅቱ ያሰበውን ኮታ ለማሟላት ሌት ተቀን ሲሰራ ቆይቷል።
የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት የዜና ምንጮቻችን እንደገለጹልን ኢህአዴግ በርካታ ሰዎችን በአንድ ለአምስት የጥርነፋ ዘዬው (ስትራቴጂ) የምርጫ ካርድ እንዲያወጡለት የፈለገው፣ በምርጫው ወቅት የምርጫ ካርድ ያወጡ ሰዎችን እንዴት አድርጎ የምርጫ ካርዳቸውን ወደ እራሱ የድምጽ ኮሮጆ የሚያስገባበትን የተጠና ዘዬ ለመተግበር ዝግጅቱን በማጠናቀቁ ነው ብለውናል፡፡
33 የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢህአዴግ አጃቢ አንሆንም በማለት ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል።
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment