እስላማዊ መንግሥት በኢትዮጵያ?
February 7, 2013
መለስ የሚሌኒየም ንግሥ እለት ተገኝተው ዘፈን ምረጡ ሲባሉ “የሱዳን ዘፈን ይሁንልኝ” ብለው ከባለቤታቸው ጋር የተምነሸነሹበት የሚሌኒየም አዳራሽ በአቶ አሊ አብዶ የከንቲባነት ዘመን ለመስጊድ ማሰሪያ ተጠይቆ እንደነበር ፣ አቶ አሊም ቦታውን ለተጠየቀው ዓላማ እንዲውል መፍቀዳቸውንና ውሳኔው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ኢህአዴግ ዘንድ መረጃው ደርሶ መታገዱን ውስጥ አዋቂዎች ያስታውሳሉ።
ከምርጫ 97 በኋላ ደግሞ መላ ሰውነታቸውን የተሸፋፈኑ ሙስሊሞች እየበዙ በመሆኑ ጉዳዩ ሥር ሳይሰድ፣ ከጀርባው እነማን እንዳሉበት ክትትል እንዲደረግ በታዘዘው መስረት የብሔራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት አስገራሚ ሪፖርት አቅርቦ እንደነበር እነዚሁ ክፍሎች ይናገራሉ። በክትትሉ የተገኘው መረጃና የመጨረሻ ድምዳሜ ተሸፋፍነው የሚለብሱት እህቶች አብዛኞቹ ሴተኛ አዳሪዎችና የገንዘብ ችግር ያለባቸው የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች መሆናቸውን ነበር።
የገንዘቡም ምንጭ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኝ አንድ የርዳታ ድርጅት ሲሆን፣ ይህንን ርዳታ ያደረገው የኢትዮጵያ ሙስሊም እህቶች አለባበሳቸው በሌላው ዓለም እንደሚዘወተረው ዓይነት ባለመሆኑ ገንዘብ በመክፈል የዕምነቱን ተከታዮች ለማደፋፈርና ተሸፋፍኖ መልበስ እንዲለመድ ለማድረግ በሚል እንደሆነ የሚጠቁሙት ክፍሎች የክትትሉ መጨረሻ ለገንዘብ ሲባል የሚደረግ የድህነት ውጤት እንጂ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊያመራ እንደማይችል የሚተነበይ መሆኑን ያስረዳሉ። በሌላ በኩል ግን ሳዑዲ የሚቀመጠው የርዳታ ድርጅት ከተወሰኑ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ሳይቀር ግንኙነት እንደነበረው፣ አቶ በድሩ አደምም በዚሁ በኩል አብረው እንደሚሰሩ ተጠቁሞ ማስተባበያ እንደሰጡበት ያስታውሳሉ።
ይህ ብቻ አይደለም በየመንደሩ የአካል ብቃት፣ የካራቴ፣ የቴኳንዶ፣ ጁዶና ተመሳሳይ ስልጠና ከሚወስዱ ወጣቶች ውስጥ ባብዛኛው ሙስሊም ታዳጊዎች እንደሆኑ መረጃ ተሰብስቦ ነበር። በአዲስ አበባ ወወክማ የሚገኝ የስፖርት ክፍል ጉዳዩ እናዳሳሰበው በመግለጽ ለፖሊስ ሪፖርት ማቅረቡም በዛው ሰሞን አጀንዳ ሆኖ ነበር። ከዚሁ ጋር የተነሳው ሌላው ቁም ነገር ገንዘብ መክፈል የማይችሉ የድሃ ቤተሰብ ልጆች ገንዘብ የሚከፍልላቸው አካል መኖሩ ነበር።
ከመጀመሪያው ግምት ስህተት በመነሳት ይሁን በሌላ መረጃ መነሻነት፣ በግልጽ ባልታወቀ መልኩ ኢህአዴግ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እምነትን ማራመድ ወይም የዕምነት ስርዓትን ማከናወን የሚከለክል ህግ አወጣ። የማንኛውም ሃይማኖት ተከታዮች በትምህርት ተቋማት ውስጥ የእምነት ስርዓታቸውን እንዳያከናውኑ በተወሰነው መሰረት በትምርት ተቋማት ውስጥ ማሸብሸብ፣ መጸለይ፣ ተሰብስቦ ወንጌል መስማት፣ ሶላት ማድረግ … ቆመ ተባለ። ይህንን መረጃ ለሌላ ጽሁፍ ስናዘጋጀው የነበር ቢሆንም ዛሬ ቀንጨብ አድርገን ያቀረብነው። የምንሰማው በሙሉ ስህተት ነው። የምንመለከተው በሙሉ ትክክል ነው ከሚል የጅምላ ድምዳሜ እንዳንደርስ ለማመላከት ነው።
በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደሚነገረው ስርዓት ጠብቀው ሃይማኖታቸውን የሚያራምዱ አሉ። ስርዓትን በለቀቀ መልኩ የግል ምኞታቸውንና ፍላጎታቸውን በሌሎች ላይ ለመጫን የሚፈልጉ አሉ። ከሙስሊሙ፣ ከፕሮቴስታንቱ፣ ከካቶሊኩ፣ ጠንቋይቤት ከሚሰግዱት፣ ሃይማኖት የለንም ከሚሉና ከሌሎችም ዘንድ እንዲህ ያለው ያልተገባ ተግባር እንደሚፈጸም በርካታ መረጃዎች አሉ። በፖለቲካው ዘርፍም እንዲሁ ነው። “እኔ የምለው ብቻ ትክክል ነው፤ እኔን ብቻ ተከተል፤ የራስህን መንገድ መከተል አትችልም፤ እኔ ባትመርጠኝም አማራጭህ ነኝ፤ እኔን አለመደገፍ ነጻነትንና ዴሞክራሲን መቃወም ነው” በሚል አቶ መለስና ድርጅቶቻቸው የሚሰሩትን ዓይነት ጥፋት የሚደግሙ አሉ። የሚለያዩትና ለተመልካች የሚያሳስቱት ሁለቱም በተጻራሪዎች በመሆናቸው ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “የኔ ሃሳብና እቅድ ይህ ነው ካመንክበት ተከተለኝ” በማለት በጨዋነት የራሳቸውን ስራና ተግባር የሚያከናውኑ መኖራቸው የሚዘነጋም አይደለም።
“እኔ ከሌለሁ አገሪቱ ሞቃዲሾ ትሆናለች” በሚል ሙሾ የሚያወርደው ኢህአዴግ ጨው እንደቀመሰ ሙክት ገንዘብና የስልጣን እድሜውን እያሰላ በሚፈጽማቸው አላስፈላጊ ተግባሮቹ አገሪቱ ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ቀውስ ተዳርጋለች። ህዝብም የሞራል ውድቀት ደርሶበታል። ከጥንስሱ ሊቋጭ የሚገባ ቀላል ጉዳይን እያነኮረ ግራ ሲገባው የድርሰትና የተወናይነት አኬልዳማዊ “ኩኩሉ” ውስጥ ተወትፎ ግራ መጋባቱን ህዝብ ላይ ያራግፋል። የሰሞኑ ድራማ የዚህ ውጤት ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ።
ጂሃዳዊ ሃረካት
አኬልዳማ የደም መሬት ማለት ነው። መቼም ኢህአዴግ የቃላትና የስም ማውጫ ማሽኑ አይደክምም “ጂሃዳዊ ሃረካት” ሲል የሰየመው ዶክመንታሪ ፊልም በራሱ ትርጉም “የጂሃድ ጦርነት” ማለት ነው።
አኬልዳማ ድርሰቱና ቅንብሩ ትኩስ በነበረበት ወቅት ሁሉም በመሰለው መልኩ አጉመተመተና የወቅቱ አዲስ ጉዳይ አረጀ፣ ተረሳ። አሁን ደግሞ የድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ከአንድ ኣመት በኋላ አዲስ ተዘጋጀ በተባለው “ጂሃዳዊ ሃረካት” በኢህአዴግ ትርጉም “የጂሃድ ጦርነት” በተሰኘ ዶክመንታሪ ፊልም የጂሃድ ጦርነት ስሜትና እስክስታ “ሰለፊያ ጁስ ቤት” ተጠነሰሰ ተባለ። አሁን ለዛሬ እስኪረሳ ትኩስ ነው። ነገ ያረጃል። በሁሉም ጉዳዮች ውስጥ ግን የማያረጁ ጉዳዮች አሉ። ለተቃዋሚም፤ ለደጋፊዎችም፤ ለገዢውም፤ ለተገዢውም።
የመጅሊስ አመራሮች ይነሱ፣ የሙስሊሙን ህብረተሰብና ሃይማኖት ተከታዮች አይወክሉም፣ እኛ አልመረጥናቸውም በሚል የተነሳው የመብት ጥያቄ በጥበብ የሚይዘው ጠፋና እየተካረረ ሄዶ እዚህ ደረሰ። የመብት ጥያቄ ያቀረቡትን የሃይማኖቱ ተወካዮችን መንግስት አሰረ። ፍርድ ቤት ክስ መሰረተ። ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዞ የመጨረሻው የፍርድ ሂደት እየተጠበቀ ባለበት ወቅት ኢህአዴግ በበላይነት በሚቆጣጠረው በፕሮፓጋንዳ ማሽኑ ኢቲቪ በኩል ባለፈው ማክሰኞ “ህገ መንግስት ይከበር ሲል፣ ህግን ሲጨፈላልቅ ታየ። ህግን ከምድሪቱ እንደ ጉም በማትነን አምባገነንነቱን አወጀ፡፡”
የጂሃድ ጦርነት ሲል ርዕስ ሰጥቶ ያቀረበው ፊልም ሲጀምር መነሻው “ድህነት” መሆኑ ከዜናው በላይ ገንዘብ እየተከፈላቸው በቀን የተወሰነ ሰዓት ተሸፋፍነው ጥቁር በመልበስ ለመኖር የሚታገሉትን ምስኪን የስርዓቱ ውጤቶች አስታወሰን። “ድህነት ለሽብር መፈጠርና መስፋፋት ዋና ምክንያት ነው” ሲል ትረካውን የጀመረው ዘጋቢ ፊልም መነሻውና መድረሻው “ኢትዮጵያን የሙስሊም አገር ለማድረግ፣ የሙስሊም መንግስት በኢትዮጵያ ለማቋቋም የተያዘ፣ በእምነት ሽፋን የሚካሄድ ነውጥ ነው” ሲል የደመደመበትን ሪፖርቱን “ሶማሊያ ድሃ አገር በመሆንዋ አልሸባብና አልቃይዳ ይህንኑ ድህነት ተጠቅመው አገሪቱን የሽብር መሬት አደረጓት” ይላል። እኛም ወደዚያ እንዳንሄድ በማስጠንቀቅ!!
“አለመታመን ታላቅ ውድቀት ነው” በሚል አስተያየት የሰጡ እንዳሉት አንድ መንግስት በብሔራዊ የአገሪቱ መገናኛ የሚሰጠው መረጃ ሁሌም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ከሆነ እውነት ቢነገር እንኳን “እንደልማዱ እየዋሸ ነው፣ ውሸት ልማዱ ነው፣ እሱን ማን ያምናል” እየተባለ በህዝብና በመንግስት መካከል መተላለፍ ይፈጠራል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መንግስት መረጃ ስለማስተላለፉና ፕሮፓጋንዳ ስለመስራቱ እንጂ ስለታማኝነት ብዙም ደንታ እንደሌለው የሚገልጹት አስተያየት ሰጪ “በዚህ አካሄድ ኢህአዴግ ሳይሆን አገሪቱ አንድ ቀን ዋጋ መክፈሏ አይቀርም” ብለዋል። አስተያየት ሰጪው ጨምረው እንዳሉት ከሆነ ስሜታዊ ሚዲያዎች የማንም ሆኑ የማን “ስጋና ደምን ረግጠው ለእውነት ብቻ ካልሰሩ አይታመኑም። ከማይታመን ሚዲያና ተቋም ይልቅ የሚዲያ ረሃብ ይመረጣል” ሲሉ ሁሉም ወገኖች ስለመታመን ሊጨነቁ እንደሚገባ ይናገራሉ።
የሳይበር ጦርነት የተካሔደበት አዲሱ የኢቲቪ “ሙቪ” እንደሚለቀቅ ይፋ ከሆነበት እለት አንስቶ ፕሮፓጋንዳውና ማስታወቂያው በማህበራዊ ገጾችና የማክሸፊያ ሚሳይል ሲወርድበት ነበር የከረመው። ፊልሙ ይፋ መሆኑንን አስመልክቶ በማከታተል የመልስ ምት የሚሆኑ “የዩቲዩብ ምርቶች” በብዛትና በዓይነት ተሰራጭተዋል። ኢህአዴግ በህግ በተያዘ ጉዳይ ላይ መግባቱና ህግን አደባባይ ላይ እንደለመደው መስቀሉ በመጀመሪያ ደረጃ ተሸናፊ ያደርገዋል። በፍርድ ቤት እግድ እንደወጣና ፊልሙ እንዲተላለፍ አይደረግም በሚል በይፋ መግለጫ ከተሰጠ በኋላ እንዲህ ያለ ተግባር መፈጸም አቶ ጁሃር መሐመድ ለኢሳት እንዳሉት በፍርድ ቤት አልሳካ ያለውን ጉዳይ ህዝብ ዘንድ በመውሰድ ጥርጣሬን መፍጠር ነው። “ውዥንብር” ማካሄድ ነው።
አነጋጋሪው አምበሉ ወይም እስማኤል አሰፋ ማን ነው?
ሃደሬ ሰፈር ከዓመታት በፊት ተከፍታ የነበረችው የሰለፍያ ጁስ ቤት ባለቤት የተባለውና በራሱ አንደበት ናይሮቢ ገብቶ “ከዳሩ ቢላል ክበብ” አባላት ጋር መገናኘቱን የገለጸው ሰው የኢቲቪ ሪፖርት እንዳለው ማን ነው? ከሁሉም በላይ አመጽን በጦር መሳሪያ በማገዝ ረገድ አልሸባብ እንዳሰለጠነው ሲናገር ተሰምቷል። በወታደራዊ ስልጠናው ክላሽንኮቭ መገጣጠም፣ የውጊያ ቦታ አያያዝ፣ የከባድ መሳሪያ ተኩስ፣ ተመሳሳይ ስልጠና መውሰዱን አስታውቋል። የመንግስትን በህዝቡና ባገሪቱ ላይ ያለውን ቁጥጥር ማሳጣት፣ ጂሃዱ እየሰፋና መንግስት ከህዝብ ጋር ሲነጠል የራስን አስተዳደር መመስረት ብሎም በመላው አገሪቱ እስላማዊ መንግስት ማቋቋም ዋናው አጀንዳ እንደሆነ ተናግሯል። ይህ የቆየ እምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ኬንያ ገብቶ የዳሩ ቢላል ክበብን ተገናኝቶ ወደ ሶማሊያ “የሽብር” ትግበራ ተምሯል።
እንደ የአውሮጳውያኑ አቆጣጠር በ1999 እንደከሰመ በተጠቆመው የኳታር ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አባል በነበሩት ዶክተር ሳላህ ነቢሃ አማካይነት ህዝባዊ ዓመጽ ስለማቀጣጠል፣ በሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አስተምህሮ የቀለም አብዮት ለማካሄድ የሚያስችል ስልጠና እንደወሰዱ ከገለጹት ጋር ተዳምሮ በኢትዮጵያ የጂሃድ ጦርነት ለማካሄድ ተደርሶባቸዋል የተባሉት ለ“ጦር ባለሙያው” አምበሉ አጃቢ ሆነው ቀርበዋል። ኢቲቪ “ስራዬን አስመልክቶ አስተያየት ሰጡኝ” ካላቸው መካከል አንድ አስተያየት ሰጪ በፊልሙ እውነትነት እንደማያምኑ አስታውቀው ለመሆኑ “አምበሉ ማን ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። አምበሉን የሚያውቁ ወደፊት ስለማንነቱ የሚሉትን ለመስማት የጓጉም አሉ።
ማንን እንመን?
በዚህ ዘገባ የቀረበውን ዶክመንታሪ ፊልም ውስጥ ምንም እውነት የለም ብለው የሚከራከሩ ያሉትን ያህል “ኢትዮጵያ በጽንፈኛ የሙስሊም አክራሪ አገሮችና ድርጅቶች ዒላማ ውስጥ ስለመሆኗ አንጠራጠርም” የሚሉ አሉ። ኢህአዴግ ለፖለቲካ ቁማር ሲል ሲፈልገው የሚለኩሰው፣ ሲፈልገው የለኮሰውን በማጥፋት ሃላፊነት የሚሰማው እየመሰለ የሚተውንበት መድረክ አድርገው የሚቆጥሩትም ጥቂት አይደሉም። አሁን ችግር የሆነው “ማንን እንመን” የሚለው ነው።
ህወሓት/ኢህአዴግንና አገርን ለይቶ የማየት ችግር በበርካታዎች ዘንድ አለ። ኢህአዴግም ጊዜያዊ የፖለቲካ ቁማርና ወደፊት የሚከተለውን መዘዝ ባለማመዛዘን የሚፈጽማቸው ስህተቶች ባንድነት ተዳምረው መጪው ትውልድ ላይ እየዛቱበት እንደሆነ የሚጠቁሙ ክፍሎች፣ ኢትዮጵያዊ ወንድማማቾች እርስ በርሳቸው ሳይሆን ከውጪ ሊገቡ በሚችሉ የተሳሳቱ ዓላማ ያላቸው “ጨዋታዎች” ውስጥ ላለመነከር መጠንቀቅ እንደሚያሻ ይመክራሉ። ወደ ልብ በመመለስ ሰክኖ መራመድ እንደሚገባ ይናገራሉ። ህወሓት/ኢህአዴግ ከህግና ከህገ መንግስት በላይ ሆኖ ስለሚፈጽመው ተግባሮቹ አብዝተው የሚኮንኑ ሁሉ “አገሪቱ ላይ የተረጨውን የብሄር ልዩነት መርዝ፣ የንቅዘት ጣጣ፣ የመበስበስ አደጋ፣ በድንገት መደርመስ አደጋ፣ በሃይማኖት ስም በየአቅጣጫው የተበተነውን ‘ጅኒ ተኮር’ ትምህርት በመለየት ሊሆን ይገባል” ይላሉ። ለጊዜያዊ ጥቅሙ እንጂ የአገራችን ዘለቄታዊ ሁኔታ ምንም የማያሳስበው ህወሃት/ኢህአዴግ በተለይ በሶማሊያ ገብቶ የፈጸመው አሰቃቂ ተግባር ኢትዮጵያን ወዳጅ እንዲበዛላት ያደረገ አይደለም፡፡ ይህንን የትላንት ድርጊት መዘንጋት እንደሌለበት የሚወተውቱ ወገኖች የሚሰጡት ማሳሰቢያ አሁን እየተካሄደ ያለውም ሆነ ወደፊት የሚደረገው ማንኛውም እንቅስቃሴ አገራችን ከገባችበት የዘርና የጎሣ አዘቅት አውጥቶ ወደሌላ ያልታሰበ አዙሪት ውስጥ የሚከታ እንዳይሆን በሰከነና በረጋ መንፈስ የወደፊቷን ኢትዮጵያን በማሰብ መሆን እንደሚገባው ነው፡፡
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment