Friday, August 30, 2013

ነሐሴ 26 በአዲስ አበባ መንግስት በጠራው ሰልፍ ያልተጠበቁ ነገሮችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል።


ነሃሴ ፳፬(ሃያ አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-  በመንግስት የሚደገፈው የሐማኖቶች ጉባኤ  በመጪው እሁድ አክራሪነት እናወግዛለን በሚል አላማ በጠራው ሰልፍ ላይ የአዲስ አበባ እና እስከ 100 ኪሎሜትር በሚደርስ ርቅት ላይ  በአጎራባች የክልል ከተሞች የሚገኙ ዜጎች በብዛት እንዲገኙ የኢህአዴግ ካድሬዎች ቤት ለቤት እየዞሩ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ሰንብተዋል።  የመንግስት ሰራተኞች ፣ በግል ስራ የሚተዳደሩ ነዋሪዎች በሰልፉ ላይ እንዲገኙ ካልተገኙ ግን አክራሪነትን እንደደገፉ እንደሚቆጠርባቸው ሲነገራቸው መሰንበቱን ወኪሎቻችንን ዘግበዋል።
መንግስት ለፖለቲካ ትርፍ ብሎ የጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ፣ መንግስትም ራሱ ያልጠበቀውን ነገር ይዞበት ሊመጣ እንደሚችል ምልክቶች እየታዩ ነው። ድምጻችን ይሰማ የተባለው አካል ከአመት ከመንፈቅ በላይ ያካሄደውን ተቃውሞ ኢህአዴግ በጠራው ሰልፍ ላይ ተገኝቶ ተመሳሳይ ተቃውሞ እንደሚያሰማ መግለጫ ማውጣቱ እሁድ ምን ይፈጠር ይሆን የሚል ጥያቄ አስነስቷል።
ድምጻችን ይሰማ ባወጠው መርሀግብር ሙስሊሙ ማህበረሰብ የሀይማኖት አባቶች ንግግር ካደረጉ በሁዋላ ነጭ ወረቀት ወይም የጨርቅ ማህረም እንዲያውለበልቡ፣  የመጅሊስ ሹሞች ንግግር ሲያደርጉ ጆሮን በመድፈን፣ ያለምንም ድምጽ ሁለት እጅን ወደ ላይ በማንሳትና በማጠላለፍ የታሰሩት የኮሚቴ አባላት እንዲፈቱ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል።
ድምጻችን ይሰማ ይህን መርሀግብሩን በተግባር ካዋለ፣ አንድ መንግስት ለድጋፍ በማለት በጠራው ሰልፍ ላይ ተቃውሞ ሲስተናገድበት በታሪክ የመጀመሪያው ይሆናል። ምናልባትም ለኢህአዴግ ታላቅ የፖለቲካ ክስረት ሊያመታበት እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
ኢህአዴግ ከውርደት ለመዳን የጸጥታ ሀይሎችን በብዛት ከማሰማራት ጀምሮ የክልል ደህንነቶች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ እያደረገ ነው።
ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው ሰልፍ ሊቀጥል እንደሚችል መታወቁ ሌላ ድራማ ሊፈጥር እንደሚችልም ይጠበቃል።
ሰሞኑን በተደረገው የሀይማኖት ጉባኤ አቶ በረከት ችግሩ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን ሲናገሩ አቶ ሀይለማርያም ደግሞ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።
 Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment