Wednesday, August 7, 2013

መንግስት የባንዲራን ክብር ያዋረደውን ግለሰብ ለፍርድ ያቅርብ!

August 7, 2013
ድምፃችን ይሰማ
ረቡእ ነሐሴ 1/2005
ሐምሌ 19 ቀን 2005 የተደረገው ዓለም አቀፍ ተቃውሞና በአዲስ አበባው ኑር መስጂድ፣ በክልል ከተሞችና በውጪ አገራት የተቀዳጀው ስኬት ያልተዋጠለት መንግስት በዚያው ምሽት በኢትዮጵያ ቴሌቪዠን ባሰራጨው ‹‹ዘገባ›› በእለቱ ተቃውሞ ሙስሊሞች የኢትዮጵያን ባንዲራ እንዳዋረዱ ገልጿል፡፡ ቴሊቪዥኑ ለተወሰኑ ሰኮንዶች ባቀረበው ቪዲዮ አንድ ግለሰብ ያረጀ እና የተቀዳደደ ባንዲራ ሲያውለበልብ ይታያል፡፡ የሚታየው ቪዲዮም ቦታው ታላቁ አንዋር መስጂድ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡Ethiopian Musilms
የኢትዮጵያ ቴሌቪዠን በመሠረቱ በ‹‹ዘገባ››ው እንዳለው በእለቱ፣ ማለትም ሐምሌ 19/2005 በታላቁ አንዋር መስጂድ እንዲካሄድ የተወሰነ ምንም አይነት የተቃውሞ መርሐግብር አልነበረም፡፡ ሕዝብም በእለቱ በአንዋር መስጂድ ሳይሆን በፒያሳው ኑር መስጂድ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ነበር መልእክት የተላለፈለት፡፡ በዚህም ምክንያት በታላቁ አንዋር መስጂድ በእለቱ ከሰላት ስነ-ስርአት ውጪ የተካሄደ ምንም አይነት የተቃውሞ መርሐግብር አልነበረም፡፡ እናም መንግስት በእለቱ በአንዋር መስጂድ ተቃውሞ ተካሂዶ እንደነበር መግለጹ የዘገባው የመጀመሪያ ሐሰት ነበር፡፡
በሌላ በኩል በእለቱ ዘገባ የተገለጸው አክራሪዎች የኢትዮጵያን ክብር በማዋረድ ‹‹እጅግ በጣም የተበጣጠሰ እና የተበጫጨቀ›› ባንዲራ ሲያውለበልቡ እንደነበር ነው፡፡ ሆኖም በተከታዮቹ ቀናት ይሄ ተለውጦ መንግስት ‹‹አክራሪዎች ባንዲራ አቃጠሉ›› ወደሚል ዘገባ ለውጦታል፡፡ ይህንንም በመቀባበል የሕገ ወጡ መጅሊስ ሹመኞችን ጨምሮ በሚዲያ የሚቀርቡ የመንግስት አፈ ቀላጤዎች ‹‹ሙስሊሞች ባንዲራ አቃጠሉ›› ወደሚል ተረክ በመለወጥ ደጋግመው ሲገልጹት ተሰምቷል፡፡ በዚህም ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ክብር እንዳዋረዱና ‹‹ለአገራቸውም ጥላቻ እንጂ አክብሮት የላቸውም›› የሚል መልእክት ለሌላው ማኅበረሰብ ማስተላለፍን መንግስት አላማው አድርጎታል፡፡
ይህን አላማውን ለማሳካት በተለያዩ ከተሞች የግዳጅ ሰልፍ ድረስ ያስወጣ ሲሆን በሚዲያም ከ10 ቀናት በላይ የዘለቀና በየእለቱ በዜናዎችና ልዩ-ፕሮግራሞች የታጀበ ሰፊ ፕሮፖጋንዳ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ሕገ መንግስታዊ ጥያቄዎችን ያነሳውንና በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ያለውን ሙስሊም ህብረተሰብ ማንበርከክ የተሳነው መንግስት ይሄን መሰል ፕሮፖጋንዳ መንዛቱ ከዚህ ቀደም ሲፈጽም የነበረውን ፕሮፖጋንዳ ለተከታተለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈጽሞ የሚገርም አይደለም፡፡ መንግስት ሰላማዊ ትግሉን ለመፈንቀል እንኳን ሙስሊሞችን በጸረ-አገርነት መፈረጅ ይቅርና ሌላም ሊፈጽም እንደሚችል የሚታወቅ ሃቅ ነው፡፡
በመሰረቱ እኛ ኢትዮጵያውያን ለአገራችን ያለን ፍቅር ከሌሎች ወገኖች ጋር የተሳሰርንበት ጠንካራ ገመድ በመሆኑ በተራ ፕሮፓጋንዳ ሊጠለሽ የሚችል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ልክ እንደሌሎች ወንድሞቹ ሁሉ ኢትዮጵያዊው ሙስሊምም ለባንዲራውና ለአገሩ ፍቅር ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱንም ከስክሶ መክፈል ያለበትን መስዋእትነት ሲከፍል ኖሯል። ‹‹መርህ ይከበር!›› ሲል ለሚጠይቀው ትግላችን እስከህይወት መስጠት የደረሰ መስዋእትነት እየከፈልን የምንገኘውም ለአገራችን ካለን ከፍተኛ ፍቅር በመነሳት ነው።
በመሰረቱ ሁለት ዓመት በዘለቀው ተቃውሟችን እንኳን እንዲህ የባንዲራን ክብር የሚያዋርድ ይቅርና የማንንም ሰላምና ጸጥታ የሚያደፈርስ ሆኖ አልፎ አያውቅም፡፡ ‹‹የተቃውሞ ንቅናቄያችን ሰላማዊ ነው›› የምንለውም በአፍ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር ነው፡፡ ንቅናቄያችን አገራዊ እና ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ስለ አገር ያለን ክብር ከሃይማኖታችን አስተምህሮ የመነጨም ጭምር መሆኑን ሁሉም ከግንዛቤ ሊከተው ይገባል፡፡
መንግስት ደጋግሞ በሚዲያ በነዛው ፕሮፖጋንዳ የሚታየውና የተቀደደ ባንዲራውን የሚያውለበልበው ግለሰብ ቅጥረኛ ግለሰብ ነው፡፡ ቀኑ በውል ባልታወቀበት የተቃውሞ ትዕይንቱ ላይ የተበጣጠሰ ባንዲራ ይዞ እንዲያውለበልብ በመንግስት ተልእኮ የተሰጠው ይህ ሰርጎ ገብ ግለሰብ ይህንኑ ባንዲራ ማውለብለብ ገና ከመጀመሩ በሰኮንዶች ውስጥ በዙሪያው የነበሩ ግለሰቦች ያስቆሙታል። ነገር ግን ይህንኑ ድራማ ለመቅዳት በአንዋር መስጊድ ዙሪያ ባሉ ፎቆች ላይ ካሜራቸውን ደግነው ሲጠባበቁ የነበሩት የመንግስት የካሜራ ባለሞያዎች ይህችኑ ለሰኮንዶች የተሳካችላቸውን ቀረጻ ህብረተሰቡ ሲከለክለውና ሲያስቆመው የሚያሳየውን ትዕይንት ቆርጠው ‹‹ሕዝቡን የሚወክል ነው›› በማለት ለፕሮፖጋንዳ በስፋት ጥቅም ላይ አውለውታል፡፡
ሆኖም ባንዲራን የማዋረድ ተግባር እኛ ሙስሊሞች አጥብቀን የምናወግዘው ተግባር ሲሆን ከመሰረታዊው የ‹‹ፍትህ ይከበር!›› ትግላችንም በእጅጉ ያፈነገጠ ተግባር ነው። ይህን ባንዲራ የማዋረድ ተግባር የፈጸመው ግለሰብ ማንም ይሁን ማን ተጠያቂ መሆን እንዳለበት እናምናለን፡፡ ግለሰቡ በግሉ በፈጸመው በዚህ የማዋረድ ተግባር ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ያለበት ሲሆን ይህንንም ሀላፊነት ሊወስድ የሚገባው መንግስት ራሱ ነው፡፡ መንግስት የተቀደደ ባንዲራ ሲያውለበልብ ለሰኮንዶች ቀርጾ ያሳየውን ግለሰብ በህግ አስከባሪዎቹ በቁጥጥር ስል ማዋልና በአገሪቱ ህግም ተገቢውን ቅጣት የማሰጠት ግዴታ አለበት። የዚህ ባንዲራን የማዋረድ ወንጀል የፈጸመ ግለሰብ ፎቶና ቪዲዮ የሚገኘው በመንግስት ሚዲያና እጅ በመሆኑ ግለሰቡ ሊሰወር እንደማይችልና በመንግስትም ጉያ የሚገኝ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ዛሬ ነገ ሳይባል ይህ ግለሰብ ፍ/ቤት ቀርቦና ጉዳዩ ታይቶ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ከማንም በላይ የመንግስት በጎ ፈቃድ አስፈላጊ በመሆኑ ግለሰቡን ለፍርድ እንዲያቀርበው አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ የግለሰቡን የፍርድ ሂደትም ተከታትሎ ለህዝብ እንዲያሳውቅ እንሻለን፡፡ የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ መሰል አጀንዳዎችን ተጠቅሞ አንድን ህዝብ በሌላው ላይ ለማነሳሳት መሞከር እጅግ አጥፊ ተግባር መሆኑንም በአጽንኦት ልናሳስብ እንወዳለን።

No comments:

Post a Comment