Saturday, August 10, 2013

ከፖለቲከኞች በላይ ገኖ የወጣው “ድምጻችን ይሰማ” ኢህአዴግ አክራሪነትን እየጋበዘ ነው!!

1


”የሰላማዊ ትግል ምንነት ለማይረዱ ትልቅ ትምህርት የሰጠ፣ ኢህአዴግ ፍጹም የሆነ ልምድ ባካበተበትና ኤክስፐርት በሆነባቸው የትግል ስልቶች ብልጫ ወስዶ ለማንበርከክ እንደሚያስቸግር፣ ሰላማዊ ትግል ከራስና ከስሜት ጋር የሚደረግ ታላቅ አስተምህሮት መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። የድምጻችን ይሰማ ትግል በዚህ መልኩ በኢትዮጵያ ቀዳሚ ሆኖ ይቆያል” በግል አድራሻ ከተላከ አስተያየት የተወሰደ።
በአሃዝ፣ ጉዳቱ በሚገለጽበት መጠን፣ ጉዳቱ የሚገለጽበት ደረጃና የቋንቋው አቅም ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ወገኖች፣ የውጪ ታዛቢዎች፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት፣ ራሱ ኢህአዴግ፣ ህወሃትና መላው ወዳጆቹ በአንድ እውነት ይስማማሉ። እሱም ህወሃት ራሱ ባመጣው ጣጣ፣ ራሱ ትዕዛዝ ሰጪ ሆኖ ያደረሰው ሰብአዊና በቀላሉ ሊበርድ የማይችል መከራ እንደሆነ በየአቅጣጫው አስተያየት እየተሰጠ ነው።
ያለ ምንም ማጋነን ኢህአዴግ ደም አፍሷል፣ ህይወት ቀጥፏል፣ አስሯል፣ ገርፏል፣ ፈንክቷል፣ ጣጣው ለሌሎች የሚተርፍ አካሄድ በመከተሉ ችግሩን አወሳስቦታል። ኢህአዴግ ይህንን ሁሉ ርምጃ የሚወስደው “ከብዙ ትዕግስት” በኋላ መሆኑን “በመንግሥት ወግ” ቢገልጽም “የሚያምነው ያገኘ አይመስልም” የሚል ወቀሳም ይሰነዘርበታል። እንደውም “ለየትኛዋ የሚወዳት አገር” በሚል ለፕሮፓጋንዳ አፉን በከፈተ ቁጥር ዘለፋ እየወረደበት ነው።

“ኢህአዴግ ጉልበት አልባ ተደረገ!”

ኢህአዴግ አቅም አልባ ሆኗል የሚሉ ወገኖች አሉ። እነዚህ ወገኖች ገለጻቸው ለሌላው ግራ የሚያጋባ አባባል ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ። ግን በነሱ እምነት ኢህአዴግ አቅም አልባ ሆኗል። አቅም አልባ ያደረገው “የድምጻችን ይሰማ” የትግል ስልት ነው። ኢህአዴግ ያለውና 4የሚታወቅበት መለያው የታጠቀው መሳሪያ፣ ወታደሩ፣ የፌደራል ሃይሉ፣ የክልል ፖሊስ፣ ፈጥኖ ደራሹ፣ የሰላምና መረጋጋቱ ፣ የስለላ ሃይሉ፣ የአጋዚ ጦሩ፣ የአንድ ለአምስት አወቃቀሩ … ከሁሉም በላይ ደግሞ ጉልበተኛነቱን የሚቆጣጠሩለት የአንድ ብሔር “ታማኝ” ሃይሎች መሆናቸው እንደሆነ አብዛኞች ይስማማሉ።3
“ኢህአዴግ አለኝ የሚለውን ጉልበቱን መጠቀም ቢፈልግም መድረኩን ‘በተጠና’ የትግል ስልት በሚፈልገው ደረጃ ሊጠቀም አለመቻሉ በደጋፊዎቹና በራሱ ዘንድ ስጋት ፈጥሯል” የሚሉት አስተያየት ሰጪ “የሙስሊሞች እንቅስቃሴ፣ የዕዝ ሰንሰለታቸውን ጠብቀው የሚያካሂዱት ትግል ኢህአዴግ ጉልበቱን እንዳይጠቀም ከልክሎታል። አሁን እየወሰደ ያለውና የወሰደው የሃይል ጥቃት ሊወስድ ከሚፈልገው ጋር ሲነጻጸር ሃይሉ ሽባ መደረጉን ያሳያል፤ ይህ ደግሞ የሰላማዊ ትግል ውበት ነው” ሲሉ ኢህአዴግ በገባው ጭንቅ መጠን ርምጃ ባለመውሰዱ እንደሚቆጭ ይናገራሉ። በሌላ አነጋገር የሽብር፣ የማሸበርና የመግደል “ጠቢብ” ለሆነው ኢህአዴግ አሁንም ችግሩ የሚፈታው በሃይል፣ በባሰ ሃይል እንደሆነ ከማመን አላፈገፈገም ሲሉ ያብራራሉ።
ኢህአዴግ ነገሮችን እያባባሰ የሰላማዊ ትግሉን ወደ አመጽ ለማስቀየር ሃሳብ ቢኖረውም “የድምጻችን ይሰማ ህብረት አስቀድሞ መረጃ የማግኘትና በሰላማዊ ትግል ተክኖ መገኘት ኢህአዴግ ያሰበውን እንዳይፈጽም አድርጎታል” በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። እነዚህ ክፍሎች ኢህአዴግ “አክራሪነትን የሚሰብኩና የሚያቀነቅኑ አሉ” በማለት ለሚለፍፈው “እስካሁን የአክራሪ ሙስሊም እንቅስቃሴ ስለመታየቱ መረጃ የለም። ከተፈጠረም አክራሪነት እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆነው ራሱ ኢህአዴግ ነው። ደም ማፍሰሱን አጠናክሮ በቀጠለና ዜጎችን ማሰሩ በገፋበት ቁጥር ለመሞት የሚዘጋጁ ዜጎች አገር ውስጥ የመኖራቸውን ያህል የወንድሞቻቸውን ጭፍጨፋ በመመልከት የመስዋዕትነቱ ተካፋይ ለመሆን ዓለምአቀፋዊ የሙስሊም ኅብረተሰብ ቁጣ ያስተባብርና ራሱን ችግር ላይ ይጥላል፤ ለአገርም መከራ ይሆናል፡፡”
በተቃራኒው አክራሪነት እየተስተዋለ የመጣው አሁን እንዳልሆነ የሚናገሩ ክፍሎች “በአሁኑ ሰዓት አገራችን ውስጥ ያለው የሃይማኖት ውህደት ቀደም ሲል እናቶቻችንና አባቶቻችን በየዋህነት ሲያደርጉት እንደነበር አይነት ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው” በማለት ይናገራሉ። በማያያዝም እንዲህ ያለው ስጋት በሰላማዊ ትግል ጉልበት አልባ የሆነውን ኢህአዴግ ሃይል እንዲያገኝና ይህንን ሃይል እንዲተማመን አድርጎታል ሲሉ ይከራከራሉ።

“ኢህአዴግ ሰክሯል”

ኢህአዴግ መስከሩን፣ አንጎሉ መዞሩንና የሚያደርገው እንደጠፋው የሚናገሩ ክፍሎች እንደሚሉት የኢድ ቀን ኢቲቪ ያሰራጨውን ዜና ቀላል ምሳሌ አድርገው ያቀርባሉ። የድምጻችን ይሰማ መነሻ ምክንያት የሆኑትን አዲሱን የመጅሊስ መሪ በቴሌቪዥን መስኮት አቅርቦ 2“ሙስሊሞች ላይ የወሰዳችሁትና የምትወስዱት ርምጃ የሚደገፍ ነው፣ ትክክል ነው” በማለት ያቀረበው ቃለ ምልልስ “ከስካርም በላይ አዙሪት ነው” ሲሉ የኢህአዴግን የበሽታ መጠን ይገልጻሉ። ሙስሊሙን አንኳን አሰራችሁት፣ ደበደባችሁት፣ ገደላችሁት በሚል ደረጃ “ደግ አደረጋችሁ፣ ርምጃችሁ ትክከል ነው” በማለት ዜና ማሰራጨቱ ኢህአዴግ በራሱ ሚዲያ በችግሩ ላይ እሳት ማርከፉን የሚያመላክት  ስለመሆኑ በማሳያነት ያቀርባሉ።
አንድ ጤና ያለው መንግስት የህዝብ ቁጣ ሳይለሳለስ፣ የቁጣውን መንስዔ አደባባይ በማቅረብ “ተጎዳን በሚሉ የህብረተሰብ፣ በተለይም የአንድ እምነት ተከታዮች ፊት ማዘፈን ኢህአዴግን የያዘውን የስካር የዞረ ድምር  (ሃንግኦቨር) የማሽተት ያህል ነው” የሚሉት ክፍሎች ኢህአዴግ ቢያንስ ለራሱ፣ ህወሃትና ቁንጮው ላይ ሆነው ሃብት ለሰበሰቡት ሲል እርቅ ሊወርድ የሚችልበትን መንገድ እንዲያስብበት ይመክራሉ። ጉዳዩንም በጥበብ እንዲይዘው ይመክራሉ።

መተማመን ድሮ ቀረ!!

በሙስሊም ወገኖች አወሊያ የተጀመረው የድምጻችን ይሰማ ጥያቄ፣ የኢህአዴግ የጥያቄው አያያዝ ችግር ተዳምሮበት የእምነቱ ተከታዮች ባሉበት ቦታ ሁሉ ተቃውሞው እየተዳረሰ ይገኛል። የአገሪቱን ሙስሊሞች ከጫፍ እስከጫፍ በሚያስገርም የግንኙነት መረብ እያስተባበረ የሚነደው ሰላማዊ ቁጣ የሌሎች እምነት ተከታዮችን ድጋፍ አለማግኘቱን ለኢህአዴግ ሃይል እንደሆነው የሚናገሩ ወገኖች “ይህንን አስመልክቶ በሚቀርበው መረጃ ግራ ተጋብተናል” ይላሉ።
“እንኳን የሌላውን ሃይማኖት የራሳቸውን ሃይማኖትና ስርዓት ማስጠበቅ ያቃታቸው የክርስትናው ሃይማኖት ተከታዮች፣ የሙስሊሙን እንቅስቃሴ ደገፉ ተብሎ ሲዘገብ ዘገባው ሚዛን የሚደፋ አይሆንም” በማለት የሚከራከሩ ክፍሎች “የክርስትና እምነት ተከታዮች ለእምነታቸው ሊሰጡ የሚገባውን ክብር ከድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ መማር ከቻሉ ይህ ብቻ በራሱ ይበቃል” በማለት በተቃራኒ ወቀሳ ይሰነዝራሉ። እንደውም የራሳቸውን የእምነት ቤት ማጽዳት ባለመቻላቸው ሊወቀሱ እንደሚገባ መረጃ በማጣቀስ ይከራከራሉ።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ላይ ካለው የረዥም ጊዜ የተቀነባበረ ሴራና የምንገኝበት የጂኦ ፖለቲካ ካሸከመን ጣጣ ጋር በማዳመር “ሜዳዎች ሁሉ ሸራተን ሆነው አይዋቡም” የሚል አስተያየት የሚሰጡ ክፍሎች “መተማመን ድሮ ቀረ” ሲሉ የሌሎች እምነት ተከታዮችን ዝምታ ይገልጹታል።
“ሙስሊሞች አብዛኞች በሆኑበት ቦታ ያለ ችግር ቢፈልጉ አክርረው፣ ቢፈልጉ አለዝበው እምነታቸውን ያራምዳሉ። አነስተኛ በሆኑባቸው አገራት ደግሞ ያለውን የአስተዳደር መሰረት የመጋራት ፈተና ይፈጥራሉ”  የሚሉት እነዚህ ክፍሎች “እነዚህ በሌሎች አገሮች የታዩ ተሞክሮዎች ከምዕራቡ መገናኛ ውስወሳ ጋር ተዳምረው በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ያስቀመጡት ጠባሳ ቀላል አይሆንም። ኢትዮጵያ ውስጥም ይህ ችግር አለ” ባይ ናቸው። በሌላም በኩል በማህበራዊ ድረገጾች አርሲ አርባ ጉጉና ጅማ የተከናወነውን በማንሳት ሰሞኑንን ለመከራከር የሞከሩትን በመጥቀስ የፍርሃቻው ማሳይ አድርገው ያስቀምጡታል።

ፍጹም ሰላማዊ ትግል – ፍጹም የሚያስቀና ህብረት!!

መሰረታዊ የእምነትና አመራር ጥያቄ በማንሳት ትግላቸውን በተጠና መንገድ የሚያካሂዱት የ”ድምጻችን ይሰማ” የትግል መስመር አስገራሚ እየተባለ ነው። ህብረታቸውና በተዋረድ የሚያካሂዱት መናበብ አስደማሚ ሆኗል። አልፎ አልፎ ከሚሰራጩ ወፍ ዘራሽ5 መልዕክቶች በስተቀር መሪዎችን በመከተል የሚያሳዩት ትብብር የሚያስቀና እንደሆነ እየተነገረ ነው። ተመሳሳይ ዓላማ ይዘው እርስ በርስ የሚቧቀሱት የተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች ከድምጻችን ይሰማ “የሰላማዊ ትግል” ቀመር ሊማሩና ይሁንታ ካገኙ ስልጠናም ሊወስዱ እንደሚገባ የሚናገሩ ተበራክተዋል።
እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት የሙስሊም ወገኖች ጥያቄና ጥያቄያቸው መልስ ካላገኘ ወደኋላ እንደማይሉ በመደጋገም ይፋ እያደረጉ ነው። ኢህአዴግ ከተካነበት ድርጅቶችን የመሰንጠቅና “የእባቡን አንገት ቁረጥ” ከሚለው የአምባገነኖች መርሁ አንጻር ድምጻችን ይሰማ ውስጥ ዘልቆ መግባት አለመቻሉ አስገራሚ የሆነባቸው ጥቂት አይደሉም። ቅንጅት እንደ ሰደድ እሳት አገር አዳርሶ ኢህአዴግን ባስጨነቀ ማግስት “ሳሎኑ ተበርግዶ ኢህአዴግ ሲንቦጫረቅበት” የተመለከቱ፤ ዓመት ከመንፈቅ ያህል የዘለቀውንና ከዕለት ወደ ዕለት በብቃትም ሆነ የኢህአዴግን መሠሪነት በመመከት እንዲሁም የተጠና የትግል ችሎታ በማሳየት ወደር ያልተገኘለትን የድምጻችን ይሰማ ትግል ከማድነቅ ወደኋላ አይሉም። ለሌሎች ሲመክሩም የመስመርና የትግል አስተላለፍ ለውጥ ለማድረግ አሁንም ጊዜው እንዳላለፈ ሊገነዘቡት ይገባል በማለት ለሌሎች የሰላማዊ ትግል ምንነት ላልገባቸውና የገባቸው መስሏቸው ተስፋ ለቆረጡ ይመክራሉ፡፡

http://www.goolgule.com/a-non-violence-beyond-politics/



1 comment:

  1. መልካሙ ሁሉ እመኝልዎታሉ አቶ ዳዊት አስመላሽ
    አንድ ነገር ለበል እንደቸርነትዎ ከሆነ ፅሁፍዎ ሁሉ <> ይደጋግማል እርስዎስ ስለትግሉ ስልትና ስለ ድምፃችን ይሰማ ምን ይላሉ? ለሃቸራችን ሰላምና ለህዝቦችዎ ደህንነትስ? ለፁሁፍዎ ግባት የተጠቀሙበት ምስል የኢድ አል ፍጥር ቀን (የአዲስ አበባ)እስቲዲየም ስለነበር የእለቱን ሁኔታ አልገለጡትምና ስለዛስ ምን ይላሉ?። መልስዎን እባክዎን።

    ReplyDelete