በዋቤ መስጊድ ማን ቦንብ አፈነዳ? ለምን?
August 4, 2013 04:32 am By
ባለፈው ዓርብ በመላው አገሪቱ አንድ ወጥ የ”ድምጻችን ይሰማ” የተቃውሞ ድምጽ ለማሰማት የወጣውን መርሃ ግብር ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ እስከ ግድያ ሊደርስ የሚችል ርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ የሚያመላክት መግለጫ አውጥቶ ነበር። የድምጻችን ይሰማ አመራር መሆናቸውን የሚገልጹት ክፍሎች ፌደራል ፖሊስ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ ተቃውሞው እንዲቀር መመሪያ ማስተላለፋቸውን ይናገራሉ። በዋቤ መስጊድ ቦንብ ያፈነዳው ማን ነው? ለምን እንዲፈነዳ ተደረገ?
ፖሊስ በከረሩ ቃላቶችና በማስጠንቀቂያ አጅቦ ባወጣው መግለጫ ” … አክራሪ ወሃቢ ሰለፊዎች ላይ ተገቢውን ክትትል በማድረጉ ፖሊስ ለሚወስደው ርምጃ ተገቢውንና የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን” በማለት አስፈራርቶ ነበር። “ምንደኛ፣ ከውጪ በሚላክላቸው ንዋይ ዓይናቸው ታውሮ አርብ በመጣ ቁጥር በተመረጡ መስጊዶች ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉ …” በማለት በመግለጫው አስቀድሞ እንደፎከከረው በኮፈሌ ብቻ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት መድረሱ ተረጋግጧል።
አስፈላጊውን ድርጊት መርሃ ግብርና የተቃውሞ ደንብ በማስተዋወቅ ከአዲስ አበባ ለአሜሪካ ሬዲዮ መግለጫ የሰጡት አስተባባሪ ኮሚቴ እንዳሉት አቶ መለስ በህይወት እያሉ በ1997 ተቃዋሚዎች ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ከሰጡት ትዕዛዝ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መግለጫ በመተላለፉ ተቃውሞው እንዲቀር ተደርጓል።
ሰላማዊ የተባለውን ተቃውሞ ከማከናወን ቢቆጠቡም ከአርብ የጁምአ ስግድት አስቀድሞ በየቤቱ በመዘዋወርና በሰላማዊ መንገድ የአምልኮ ስርአታቸውን ለመፈጸም ወደ ተለያዩ መስጊዶች ካቀኑ ምዕመናን መካከል ቀላል ቁጥር የሌላቸው ታስረዋል። ለቪኦኤ መግለጫ የሰጡት የድምጻችን ይሰማ ተወካይ ካንድ ሺህ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን አመልክተዋል።
ከመንግስትና የድምጻችን ይሰማ አስተባባሪ ነን ከሚሉት አካላት የሚወጡትን መረጃዎች ሁለት ጽንፍ የያዙ በመሆናቸው በማጣራትና አግባብነት ያለው ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት የዝግጅት ክፍላችን ተቸግሯል። በዚህም የተነሳ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት እንዳለ ሆኖ ባብዛኛው ዘገባችን ከማህበራዊ ገጽ በሚገኙ ዜናዎችና ከመንግስት ድረገጾች እንዲሁም ከአሜሪካ ሬዲዮ ባገኘነው መረጃ የተወሰነ ሆኗል።
በኦፊሴል በማይገለጹ አድራሻዎች፣ በፌስቡክ፣ በተለያዩ የማህበራዊ አምዶችና ድረገጾች በየአቅጣጫው የሚወጡ ዘገባዎች እንዳሉ ሆነው፣ የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ አስመልክቶ መረጃ የሚሰጠው “ደምጻችን ይሰማ” የማህበራዊ ገጽ በምዕራብ አርሲ ኮፈሌ ልዩ ስሙ ዋቤ በሚባል ቦታ የመንግስት ታጣቂ ሃይሎች በወሰዱት ርምጃ የሟቾችን ብዛት አስራ አንድ እንደደረሰ አስታውቋል። ዘገባው ከሞቱት መካከል አንድ ህጻንና ሴት ይገኙበታል ብሏል።
የሲኤንኤን የአይን ሪፖርተር ደግሞ በተመሳሳይ ቀን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች 25 ሰዎች መገደላቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን አስነብቧል። ዜናው ከ1500 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ያመለከተ ሲሆን፣ ከሟቾቹ መካከል አንድ ህጻን አንደሚገኝ የአይን እማኙን በመግለጽ አመልክቷል።
የአሜሪካ ሬዲዮ ዘጋቢ የአካባቢውን ነዋሪዎች በምንጭነት ጠቅሶ እንደዘገበው ሀምሌ 26 ቀን 2005 ዓ ም የተከሰተው ግጭት መንስዓው በዋቤ መስጊድ ፖሊስ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል መጀመሩን ተከትሎ ነው። ህዝቡ የፖሊስን ድርጊት እየተቃወመ ሳለ በድንገት ቦምብ መፈንዳቱን ዘገባው አመልክቷል። ቦንቡን ከህዝብ ወገን የሆኑ እንዳላፈነዱትና ቦምቡ እንደፈነዳ ፖሊስ ጥይት በመተኮስ ሰዎችን መግደሉን ያስታወቀው የቪኦኤ ዘጋቢ፣ አስራ ሁለት የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን ተናግሯል። የስድስቱን ሟቾች ስም ዝርዝር አስታውቋል። 1ኛ፣ ቱርኬ ሳቶ 2ኛ፣ መሐመድ ሃሰን 3ኛ፣ ሌንጮ 4ኛ፣ ኩርሴ ቱራ 5ኛ፣ ረሺድ ቡርቃ፣ 6ኛ፣ ሳፊ ቴሲሳ በየተራ ዘርዝሯል። ቦንብ ማፈንዳቱ ለምን እንደተፈለገ ዝርዝር መግለጫ አልተሰጠበትም።
በኮፈሌ የደረሰውን አደጋ አስመልክቶ ውስን ሪፖርት ያቀረበውና የመንግስትን አካላትን ለማነጋገር እንዳልቻለ ያመለከተው ይኽው ዘገባ፣ በስተመጨረሻ አገኘሁት ባለው ዘገባ መሰረት የቁስለኞች ቁጥር ሰላሳ አምስት መድረሱን ዘግቧል። መንግሥት ሶስት ሰዎች መሞታቸውን ከማስታወቁ በስተቀር ተጨማሪ ያለው ነገር የለም። ከዚህ በተቃራኒ “የሙስሊሙ ህብረተሰብ አክራሪዎች የፈጸሙትን ድርጊት ተቃወሙ” የሚል ዜና አሰምቷል።
ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሻሸመኔ ፖሊስ ዘንድ ደጋግሞ በመደወል የተጣራ መረጃ ማግኘት ባይችልም የሟቾቹ ቁጥር መንግስት እንዳለው ሶስት ሳይሆን ዘጠኝ እንደሚደርስ ስማቸውን ካልገለጹ የፖሊስ አባል መረጃ አግኝቷል። አባሉ ይህ መረጃ በአርሲ ኮፈሌና አካባቢው ብቻ የደረሰ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ግምት አላቸው።
የእንቅስቃሴው መሪ ከሆኑት መካከል የሚጠቀሰው ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ በድምጽ ያስተላለፈው ዘገባ ሰዎችን በማነጋገር ጭምር ነበር። በዘገባው የእምነቱ ተከታዮች “ትዕግስታችን አልቋል” ማለታቸውንና “መስጊድ በጥይት ተበሳሳ ድረሱልን” የሚል መልዕክት ለጥንቃቄ በሚመስል መልኩ ማንነታቸውንና አድራሻቸውን ካልገለጹ አስተያየት ሰጪዎች በድምጽ አሰምቷል።
“ኢማሞቻችን አትሰሩ፣ ሐይማኖታችንን ለኛ ተው” በማለት ቅሬታቸውንና ተቃውሟቸውን የሚገልጹትን ለማፈንና ርምጃ ለመውሰድ መንግስት ከፍተኛ በሚባል ደረጃ የአጋዚ፣ የፌደራልና ፖሊስና የኦሮሚያ አድማ በታኝ ፖሊስ ሃይል ማሰማራቱን ጋዜጠኛ ሳዲቅ ያነጋገራቸው ምስክርነት ሲሰጡ ለማዳመጥ ተችሏል።
በሙስሊም ሰላማዊ ሰላፈኞች ላይ የደረሰውን አደጋ ደምጻችን ይሰማ እንደሚከተለው አቅርቦታል።
ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂኡን!በኦሮሚያ አርሲ ዞን የሟቾች ቁጥር 11 ደርሰ!
ትናንት ማለዳ ጀምሮ የመንግስት ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ገብተው በሰነዘሩት ጥቃት የሟቾች ቁጥር 11 ደረሰ፡፡ ከሻሸመኔ እስከ ኮፈሌ እና ዶዶላ ድረስ በሚያካልለው በዚህ የመንግስት ወታደሮች ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው እና የታሰሩ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል፡፡ በእለተ ቅዳሜ ምንም አይነት ተቃውሞም ሆነ መሰል እንቅስቃሰሴዎች በማይካሄድበት እና ባልተካሄደበት እለት የመንግስት ወታደሮች እስከገጠር ቀበሌዎች ድረስ ዘልቆ በመግባት ያለርህራሄ የቀጥታ ጥይት በመጠቀም የአካባቢውን ዜጎች ሲገድሉ ውለዋል፡፡
የመንግስት ቴሌቪዥን በተለመደ መልኩ ‹‹ጂሀድ ሲቀሰቅሱ እርምጃ ተወሰደባቸው›› የሚል ዜና ያሰራጨ ሲሆን የሞቱት ሰዎች ቁጥርም 3 ብቻ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ መንግስት ቀድሞ በታሰበበት መልኩ በአካባቢው ከፍተኛ የወታደር ሰፈራ በማድረግና በተጠንቀቅ በማስቆም በፌዴራል ፖሊስ፣ አድማ በታኝ እና በወታደሮች በመታጀብ በአካባቢው ሕዝብ ላይ ከማለዳ ጀምሮ ጥቃት ሰንዝሯል፡፡ አራት ኦራል መኪኖች ላይ የተጫኑ ወታደሮች አካባቢውን በመክበብ መስጂዶች እና መኖሪያ ቤቶች ላይ ጭምር ጥይት ሲተኩሱ እንደነበር የታወቀ ሲሆን በዚሁም የአካባበውን ታዋቂ የሃይማኖት መምህር፣ አንዲት ሴት እና ህጻን ልጅን ጨምሮ የሟቾች ቁጥር 10 ደርሷል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የራሳቸውን መኪና መስታወት በመሳሪያ ሰደፋቸው በመስበር ‹‹ሕዝቡ ሰበረው›› የሚል ፕሮፖጋንዳ ለመስራት የሚያስችል ጥረት ሲያደርጉም ታይተዋል፡፡
መንግስት ምላሽ መስጠት የተሳነውን ሕገ መንግስታዊ የህዝብ ጥያቄ በጥይት በዚህ መልኩ ምላሽ ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ባለፈው አመት በአርሲ ዞን አሳሳ ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽሞ አራት ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል፡፡ ከዚያም በመቀጠል በአማራ ክልል ገርባ ከተማና በሐረር ኢማን መስጂድ ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽሞ በድምሩ ከ13 ሰዎች በላይ ህይወታቸው በመንግስት ታጣቂዎች ጥይት ተቀጥፏል፡፡ መንግስት የገደላቸውን ሰዎች በሙሉ ‹‹ለጂሃድ ሲያነሳሱ ገደልኳቸው›› የሚል ማስተባበያ ሲሰጥ ቢቆይም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ አሁንም ይህ የመንግስት ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ቀጥሏል፡፡
አሁንም ሙስሊሙ ኅብረተሰብ መንግስት ሊፈጥር እያሰበ ያለውን ተጨማሪ ኹከት በመገንዘብና ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ በማሰብ የመንግስትን ትንኮሳ ቸል እንዲልና በትእግስት እንዲያሳልፍ አስቸኳይ መልእክት እናስተላልፋለን፡፡ የመንግስት ቀዳሚው ፍላጎት መጀመሪያ እንደታየውም ኹከትና ግጭት በመፍጠርና ጥፋት በማድረስ፣ ሙስሊሙን ኅብረተሰብ ለመወንጀልና ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ለመጠቀም በመሆኑና ይህም በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ በመሆኑ፤ መንግስት ኹከት ሲቀሰቅስ በቸልታና አይቶ በማሳለፍ በመንግስት ወጥመድ ላለመውደቅ ሁሉም ጥረት እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡ ከምንም በላይ ሰላማዊነታችን ዋጋ የምንሰጠው መሆኑን ሁላችንም ከግንዛቤ በመክተት ሰላማችንን ሊነጥቁ የሚመጡ ኃይሎን በሰላም ብቻ እነድንመልሳቸው አደራ እንላለን፡፡
አላሁ አክበር!
መንግስት በበኩሉ በተቃራኒው “በኦሮሚያ ክልል ኮፈሌ ከተማ አክራሪ ሃይሎች ጉዳት አደረሱ” ሲል ነው ሶስት ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ያመነበትን ዜና ያሰራጨው።
በኦሮሚያ ክልል ኮፈሌ ከተማ አክራሪ ኃይሎች ጉዳት አደረሱ
በኦሮሚያ ክልል ኮፈሌ ከተማ ዛሬ አክራሪ ኃይሎች በፈጠሩት ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ በሰውህይወትና ንብረት ላይ አደጋ መድረሱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በምዕራብ አርሲ ዞን በኮፈሌ ወረዳ ኮፈሌ ከተማ ውስጥ ዛሬ ሀምሌ 27/2005 አክራሪ ኃይሎች በፈጠሩት ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ አደጋ መድረሱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የሽብር እንቅስቃሴው በፖሊስና በህብረተሰቡ ትብብር በቁጥጥር ስር መዋሉንም የኦሮሚያ ፖሊስኮሚሽን ጨምሮ አስታቋል፡፡ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ የእስልምና እምነትን ሽፋን በማድረግ ህዝብን የመከፋፈልና ሰላምን የማደፍረስ አጀንዳ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ አክራሪና ፅንፈኛ ቡድኖች በዛሬው ዕለት ከጧቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በምዕራብ አርሲ ዞን ዋቤ ከተማ የጀመሩት ሁከት ወደ ኮፈሌ ከተማ በመሸጋገሩ ፀጥታ ለማስከበር በተሰማራው የአካባቢው የፖሊስ ኃይልና በሁከቱ ተሳታፊዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት የሶስት ሰው ህይወት ማለፉና በሰባት የፖሊስ አባላት ላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ መድረሱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
በአክራሪ ቡድኖች ተቀናጅቶ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማወናበድና ለሁከት በማነሳሳት ኮፈሌ ከተማ ላይ በዛሬው ዕለት ተቀስቅሶ በሰላም ፈላጊ የአካባቢው ህዝብና በፖሊስ ኃይል በቁጥጥር ስር የዋለው ይህ የሁከት ድርጊት አክራሪ ኃይሎች ከዚህ ቀደም በ2004 ዓ.ም በዚያው ዞን ገደብ አሳሳ ላይ ጁሃድ በማወጅ ሞክረውት ከነበረው የጥፋት እንቅስቃሴ የቀጠለ ነው፡፡
በኮፈሌ ከተማ በዛሬው ዕለት የተቀሰቀሰው የአክራሪ ኃይሎች የሁከት እንቅስቃሴ በሰላም ፈላጊው የአካባቢው ህዝብ ትብብርና በክልሉ ፖሊስ ኃይል በቁጥጥር ስር የዋለ ቢሆንም ጽንፈኞች ኃይሎቹ ህገ መንግስቱን በመጻረር የህዝብን ፀጥታ ለማወክና በሰላዊ ዜጎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የጀመሩትን እንቅስቃሴ ለማምከንና የጥፋቱ አቀናባሪና ፈጻሚ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከመቼውም በላቀ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጾ ሰላም ወዳዱ ህዝብ ከመንግስት ጋር በመሆን አጥፊዎችን በማጋለጥና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪውን አቅርቧል።
ከመንግስት ወገን ከላይ እንደተገለጸው ቢቀርብም በአካባቢው መረጋጋት እንደሌለና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መታሰራቸው ታውቋል። በከባድ የወታደራዊ ተሽከርካሪዎች የሚጓጓዙት ታጣቂ ሃይሎች ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር መግባባት እንዳልቻሉ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ በአካባቢው አንጻራዊ መረጋጋት ስለመስፈኑ ከገለልተኛ ወገን የተባለ ነገር የለም። ይልቁኑም ከአያያዝ ጉድለት እየተካረረ የመጣውን የሙስሊሞች ጥያቄና ባገሪቱ እየጠነከረ የመጣውን የጥላቻ ፖለቲካ አገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራት ስጋታቸውን የሚገልጹ ተበራክተዋል።
ዓመት ከመንፈቅ ያስቆጠረው የድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ በግብጽ እንደታየው የአረብ ጸደይ የበርካታውን ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ድጋፍ ያገኘ ባይሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ዘንድ አድማሱን እያሰፋ መሄዱና መንግስትም ከቀን ወደ ቀን የሃይል ርምጃ መምረጡ በአገሪቱ ካለው በርካታ ፖለቲካና የማህበራዊ ችግች ጋር ተዳምሮ አገሪቱን ለከፋ አደጋ እንዳይዳርጋት ስጋት አንዳላቸው የሚገልጹ ክፍሎች “ሁሉም ወገኖች ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡና ችግሩን በሰላም ለመፍታት የሚችሉበት አግባብ ሊፈጠር ይገባል” ብለዋል። የክርስቲያኑ ኢትዮጵያዊ ግልጽ ድጋፍ አለመታየት የድምጻችን ይሰማ ጥያቄዎች (የመጅሊስ አመራር፣ የአህባሽ ጉዳይ፣ …) ሃይማኖታዊ በመሆናቸው ይሁን ወይም ሌላ ምክንያት በግልጽ የታወቀ ባይሆንም በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ ኃይላት ሁኔታው ወደ አረብ ጸደይ እንዲቀየር ገና ከጅምሩ ጥሪ ሲያስተላልፉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን በዚህ ሃሳብ ዙሪያ በተከታታይ የሚመለከታቸውንና ያገባናል የሚሉ ዜጎችን አስተያየት እንዲሰጡ በመጋበዝ በእርቅ አስፈላጊነት ላይ ተከታታይ ዘገባ እንደሚያቀርብ ከወዲሁ ያስታውቃል። ከዚህ በፊት በግልጽ እንዳስታወቅነውም አስተያየት ያላቸው ወገኖች በነጻነት ሃሳባቸውን እንዲሰነዝሩ ይጋብዛል። ከጉዳዩ አሳሳቢነትና አገራችንን ከማስቀደም አንጻር ለሚቀርቡ አስተያየቶች ማናቸውንም ገደብ የማናደርግ መሆኑንን ከወዲሁ እናስታውቃለን። ህዝብ ሊያውቅ የሚገባውን ሁሉ ማወቅ ይገባዋል፤ አገር ከሌለ ማንም ሊኖር አይችልም! (Photo: CNNiReport)
Posted Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment