ኢሕአፓ ወክንድ ሰኔ ፪፯ እና ፪፰ ባካሄደው በዚህ አራተኛ ጉባዬው ሐገራችን የምትገኝበትን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ፣ የውስጥና የውጭ ሀይሎች የሕዝቧን አንድነትና አይበገሬነት ለማዳከም ብሎም ሉዓላዊነቷን ለመድፈር የሚሸርቡትን ሴራ በጥንቃቄ መርምሯል። ከዚህም በማያያዝ ኢሕአፓ ወክንድ በሰማያዊ ፓርቲ በር ከፋችነት በሐገር ቤት ያሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች ከቅርብ ቀን ወዲህ የወያኔን አፈና ሰብረው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው ሕዝባችን በተለይ በወያኔ የግፍ አገዛዝ ላይ ያለውን ተቃውሞ እና ለለውጥ ያለውን ተነሳሽነት አደባባይ ወጥቶ በተቃውሞ ሰልፍ እንዲያሳይ በመጥራታቸው እና የተቃውሞ ሰልፉቹም በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቃቸው ለበለጠ የተቀናጀ ትግል የሚያነሳሳ ነውና ሁለገብ ጸረ ወያኔው ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያልተገደበ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁነቱን አረጋግጧል።
የኢሕአፓ ወጣት ክንፍ ድርጅት ከተቋቋመበት ወቅት ጀምሮ ቀደምት አባቶቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን እና እናቶቻችን ለተሰውለት ሐገራቸንን ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ትግል ሳያሰልስ አስተዋፅዖ ሲያደርግ ቆይቷል። ይህ ቀጣይነት ያለው ትግል ብዙ መሰዋዕትነትን የጠየቀ ቢሆንም ወደፊትም ለሚከፈለው መስዋዕትነት ኢሕአፓ ወክንድ ከመቼውም ግዜ ይበልጥ ዝግጁ ነው። ኢትዮጵያችን አድጋና በልጽጋ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት መብቱ ተከብሮ የሚኖርባት ሐገር ስትሆን የማየት ራዕይ ሰንቀው እኛ ብናልፍም ጓዶቻችን ዳር ያደርሱታል፣ ታጋይ ይሞታል አንጂ ትግል አይሞትም፣ ኢሕአፓ ያቸንፋል!! እያሉ መተክያ የሌለውን ሕይወታቸውን የሰዉትን ብርቅዬ የሕዝብ ልጆች የትግል አርማቸውን ከፍ አድርጎ፣ በደምና በአጥንት የተገነባ አኩሪ ታሪካቸውን ጠብቆ ትግሉን ለማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለበት በማመን የኢሕአፓ ወጣት ክንፍ ድርጅት አራተኛውን ጉባኤውን ባጠናቀቀብት እለት የትግል ቃል ኪዳኑን አድሷል።
ኢሕአፓ ወክንድ በዚህ ጉባኤው በውጭ የሚገኙ ጸረ ወያኔ ተቃዋሚ ድርጅቶች በሙሉ ሀይላቸውን በማስተባበር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው ዴሞክራሲያዊ አደረጃጀት ሁሉንም ዜጋ አሳትፎ የሕዝብ የስልጣን ባለቤትነት እንዲከበር፣ የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና የሕዝቧ አንድነት ተጠብቆ የእምነት ነጻነት አንዲረጋገጥና በአጠቃላይ የወያኔ ስርአት ተወግዶ በሕዝባዊ ሥርዓት እንዲተካ በሐገር ቤት ከሚገኙ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በተቀናጀ መልኩ መታገል አማራጭ የማይገኝለት አግባብ መሆኑን በአጽንኦት የሚቀበለውና ለተግባራዊነቱም በግንባር ቀደምትነት የሚሰለፍ መሆኑን አረጋግጧል።
ኢሕአፓ ወክንድ ዛሬም አንደትላንት እራሱን አንደ አንድ አማራጭ ኃይል ለስልጣን ባለቤቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እያቀረበ ለሕዝብና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከሚታገሉ ሀይሎች ጋር ከድርጅት አጥር ይበልጥ ኢትዮጵያዊነትን በማጥበቅ በውጪ የምንገኝ ሁሉ እንዴት በሐገር ቤት ካሉት ወገኖቻችን ጋር በመተባበር የጋራ መድረክ ፈጥረን፣ ለምን ነገ ዛሬ ሳንል በአንድነት መነሳት አንደሚገባን በስፋት ተወያይቶ የሚከተሉትን ነጥቦች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በሙሉ በጽሞና ሊመለከቷቸው ይገባል ይላል።
፩. ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው ምሁራን በወያኔ ጣልቃ ገብነት በነፃነት መስራት ባለመቻላቸው ሐገር ጥለው እየተሰደዱ መሆኑን።
፪. የአንድ ሐገር የኢኮኖሚ ምሶሶ የሆነው ሐገር በቀል የንግድ ማህበረሰብ በኢንቨስተር ስም የሚመጡ ባዕዳንና የወያኔን የንግድ ኩባንያዎች ገደብ ያጣ አድሎአዊ ተጽእኖ የተነሳ ስራ መስራት ባለመቻሉ ሐገር ጥሎ እየተሰደደ መሆኑን።
፫. ለአንድ አገር የጀርባ አጥንት የሆነው ወጣት ሐገሩን ጥሎ እየወጣ መሆኑን፣ ያልቻለ ደግሞ የሱስ ተገዥ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን።
፬. ጋዜጠኞችን ወያኔ ሆን ብሎ እያዋከበ፣ እያሰረ፣ እየገደለ የተረፉትንም ከሐገር እንዲወጡ እያደረገ መሆኑን።
፭. የኢትዮጵያ የመምህራን ማህበር፣ የሰራተኛ ማህበር፣ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች በአጠቃላይ በሐገሪቱ እድገት፣ ሉዓላዊነት፣ የዴሞክራሲ ግንባታ ጉልህ ሚና ሊኖረው የሚችለው ዜጋ ሁሉ ከሐገሩ እየወጣ በምትኩ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ለአንድነት አስጊ የሆኑ ባእዳውያንና የአንድ ዘር ምርጥ ቡድን አባላት የበላይነት በኢትዮጵያ ሐገራችን ተንሠራፍቶ መገኘቱ ሐገራችንን መስቀለኛ መንገድ ላይ ያደረሳት መሆኑ ኢሕአፓ ወክንድን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳስቦታል። በመሆኑም ኢሕአፓ ወክንድ ከዚህ በመነሳት የተቃዋሚ ድርጅቶችንም አሰላለፍ አጽንኦት ሰጥቶ ተመልክቷል።
፮. ሕዝባችንን ሆን ብሎ ለመከፋፈልና ለማዳከም ብሎም ለወያኔ መሰል ጎጠኛ ጠባብ ቡድን አባላትና ለባእዳን ጠላቶቻችን የዘመናት ተገዥና ባርያ ለማድረግና ሕዝባችን በግፍና በመከራ እየማቀቀ መብቱ ተረግጦ እንዲቀጥል የሚደረጉ ስውርና ግልጽ ሴራዎችን ነቅቶ ማጋለጥና መታገል የሁሉም ኢትዮጵያዊ የዜግነትና የታሪክ ግዴታ መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የማይገባ መሆኑን።
ኢሕአፓ ወክንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ልዩነታቸውን አቻችለው እራሳቸውን አንደ አማራጭ በማቅረብ አላማቸውን ለሕዝብ ቀርበው በግልጽነት በማስረዳት ሕዝባዊ ውሳኔን በጸጋ የሚቀበሉበትን ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለመገንባት በወያኔ እየተገፋ ከሐገሩ የወጣውን ወገን እንደየእውቀቱና እንደየተሰጥዖው ለሐገሩ እና ለሕዝቡ ማበርከት የሚጠበቅበትን የዜግነት ግዴታውን ሊወጣበት የሚችልበት መድረክ እስካልፈጠሩና እስካልከፈቱ ድረስ ለሐገራችን ችግር ፈጣሪ ባይሆኑም ለችግሩ መፍትሄ ሰጪ ሊሆኑ ባለመቻላቸው ከታሪክ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ማስገንዘብ ይወዳል።
ስለዚህ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ወያኔን በማንኛውም መንገድ መታገል የሚፈልገውን ወገን ዛሬ እንደችሎታውና እንደተሰጥኦው አሰልፈው ማታገል ይጠበቅባቸዋል። ኢሕአፓ ወክንድም ይህን ትልቅ አቅምና እውቀት ያለውን ሐገር ወዳድ ሀይል አሰባስቦ ለማታገል ቆርጦ ከተነሳ ወገን ጋር በሐገር ቤትም ይሁን በውጭ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የተላበሰ ሁሉንም ሐገር ወዳድ የሚያሳትፍ ሥራ በመስራት ከአሁን ቀደም በተግባር ያሳየውን አንቅስቃሴ ከመቼውም ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠል ውሳኔዎችን አሳልፎአል።
የሐይማኖት ነጻነት አንዲከበር፣ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ እንዲፈቱ፣ በተለያዩ የሐገራችን ክፍሎች በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የሚደረገው የይዞታ ማፈናቀል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ግፍና ሰቆቃ እንዲያበቃ፣ የወያኔ ወንጀለኞች ካባቸውን በመቀየር የተቃዋሚ ድርጅት መሪ መስለው መቅረብ ሲሞክሩና የሐይማኖት ቤቶቻችንን በታጣቂዎችና የበግ ለምድ በለበሱ ተኩላዎች መውረር ሲቃጡ በግንባር ተሰልፎ በማጋለጥና በመመከት፣ ዘንድሮ ፴ኛ ዓመቱን ያከበረውን የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽን ከወያኔ ስውርና ግልጽ ደባ ጥቃት ለመመከት ከህዝብ ጎን በመሰለፍ ያደረገውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለወገኖቻችን እያበሰረ ይህን ኃላፊነት ወስደው በብቃት ታግለው ላታገሉን አመራሮቻችን አይበገሬነትና ውድ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ይህ ጉባኤ ስራችሁ ምስክራችሁ ሆኗልና ለአሉባልተኞች ቦታ ሳትሰጡ በያዛችሁት የድል ጎዳና ግፉበት ይላል።
ከኛ በፊት በክብር ባለፉ ጀግኖች ስጋ፣ ደምና አጥንት እንዲሁም መተኪያ በሌለው የሕይወት መሰዋትነት ተከብራና ታፍራ የኖረች ውድ ሐገራችንን፣ በሰላም በፍቅርና በመተሳሰብ አንድነቱን ጠብቆ፣ ተዋዶ፣ ተጋብቶ፣ ተዋልዶ፣ ተሳስሮ፣ ለብዙ ሺ አመታት የኖረው ሕዝባችንን፣ ወያኔና የውጭ ጠላቶቻችን እንዲሁም ዘመን አፈራሽ በታኝ ባንዳዎች “የፖለቲካ ተንታኞች” የሚያካሂዱት ግልጽም ሆነ ስውር ሴራና ገደብ ያጣ ግፍ ከአቸናፊነት እንደማይገቱት አለመገንዘብ ታሪክ አራሷን አንድምትደገም መዝንጋት ወይም እብድነት መሆኑን ልብ በሉ ይላል::
ኢሕአፓ ወክንድ ደርሶ በሕዝባችን ደም መነገድ ለሚሹ፣ “ዘመናዊ” ባንዳዎች ከሕዝብና ከታሪክ ተማሩ ይላል። ታሪክ እራሷን ትደግማለችና፣ ዛሬም ኢትዮጵያ የአልፍ አእላፍ ጀግኖች ሐገር ናትና! ዛሬም ለጸረ ኢትዮጵያዊነት ማርከሻው ኢትዮጵያዊ አንድነት ነውና! በባእዳን፣በወያኔና በዘመናዊ ባንዳዎች በተቀደደልን ቦይ እንደውሃ በመፍሰስ በዘር በሐይማኖት ወዘተ ተከፋፍለን የመከራ ዘመናችንን ለማራዘም የማንመች የባንዳ ሳይሆን የጀግኖች ልጆች ነን የሚሉትን አይበገሬ አንበሶች ካላቸው የትግል ተመክሮ የሕዝብ ወሳኝነትን አስቀድመው ለወገንና ለሀገር የመስራት ብቃት አንጻር በአሁኑ ወቅት በሕቡእ አና በግልጽ እየሰሩ ያሉ አመራሮቻችንን ለሚቀጥሉት ሁለት አመታት በአመራርነት እንዲቀጥሉ ጉባኤዬው ከመወሰኑም በላይ በሀገር ቤት በሕቡዕ ከሚንቀሳቀሱ አመራሮቻችን በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካም ትግሉን ለማቀላጠፍ የጋራ አመራር አካል ተመስርቷል። ይህንንም አካል እንዲመራ በዚህ የወክንድ ፬ኛ ጉባኤ ጎድ ይማም ተመርጧል።
ትግሉን ለማስቀጠል በጉባኤው የተመረጡት አመራሮች፥
፩. ይማም
፪. በላይ
፪. ድሪባ
፫. ፍሬ ጽድቅ
፬. ታዘበው
፭. ብሩክ
ለነዚህ የአመራር አካላት በሐገርቤት በህቡዕ፣ በውጪ በይፋ የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ እስካላሰገቡ ድረስ ማንኛውንም ፀረ ወያኔ ትግል በጋራ ለማስቀጠል ከሚፈልጉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ውይይት ምክክር ሊያደርጉ የሚያስችል ኃላፊነት ኢሕአፓ ወክንድ ሰጥቶአቸዋል።
ኢሕአፓ ወክንድ በቀጣዩ የትግል ጊዜ፣ በኢትዮያዊነት የሚያምን ዜጋ ሁሉ ሐገራችንንና ሕዝባችንን የዲሞክራሲ የፍትህ የሰው ልጅ በዘሩ ሳይሆን በሥራውና በእውቀቱ የሚከበርበት፣ ሁሉም በነፃነት የሚኖርበት ሐገር እንድትኖረን ለምናደርገው ትግል ዛሬ ያለንን ቅራኔና ልዩነት አቻችለን የሕዝብን ውሳኔ ሰጭነትና የስልጣን ባለቤትነት አምነን ተቀብለን ወያኔንን ማስወገድ ካልቻልን ነገ ከነገ ወዲያ የምናደርገው ትግል ከዘረኛው ወያኔ ጋር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት እየዘረፈ ገበሬውን ከመሬቱ በኢስቨስተር ስም እያፈናቀሉ ኢትዮጵያ ሐገራችንን የሸቀጣቸው ማራገፍያ ካደረጎት ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከሳውዲ ጋር ይሆናል። ትግሉም ከዴሞክራሲ ትግል መርሕ በተጨማሪ የሐገር ባለቤትነት ትግል ይሆናል። አንድ ዘረኛና ጠባብተኛን የሕዝብ መሰረት የሌለውን ወያኔን በጊዜ ተቻችለን ማስወገድ ሳንችል ቀርተን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ከእኛ ለሚቀጥሉት ትውልዶች እኛ ከወያኔ ነፃ ያላወጣናትን ሐገር በማስረከብ እነሱ ከቻይና ከህንድና ከአረብም ነፃ እንዲያወጧት ውስብስብ ትግል ትተንላቸው እንዳናልፍ ደግመን ደጋግመን ልናስብበት ይገባል እንላለን።
በዚህ ወሳኝ ትግል፣ በዚህ የታሪክ አጋጣሚ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከኛ በፊት በነበረው ትውልድ መስዋአትነትና ጀግንነት የቆየችንን ሐገር ጠብቀን ለተተኪው ትውልድ የማስረከብ ግዴታችንን መወጣት ከተሳነን፣ ልጆቻችን በኛነታችን የሚያፍሩ፣ የተናቁ፣ ሐገር አልባ ዜጎች ከመሆን አያልፉም። ግና የታሪክ አደራችንን ከመወጣትም አልፈን አንድ እርምጃ ወደፊት በመሄድ የአንባገነኖችን በሕዝባችን ጫንቃ ላይ መፈራረቅን ለማስቆም፣ የሕዝብን የነቃ ቀጣይነት ያለው ተሳትፎ በማረጋገጥ የድርጅት መሪዎችን፣ ፖለቲከኞችን፣ የመንግሥት ባለስልጣኖችን፣ የሐይማኖት መሪዎችን፣ ምድራዊ ሲኦልን በህዝባችን ላይ የሚያውጁ ጠያቂ የሌላቸው አምባገነኖች ከመሆን ለመግታት የሚያስችል መሰረት ጥለን ብናልፍ ታሪክ ለዘለዓለም አንደሚዘክረን ጥርጥር የለውም። ሕዝብ የስልጣን ባለቤት በመሆን ያሻውንና የሚበጀውን የሚመርጥበት ስርአት ተመስርቶ ግልጽነት ተጠያቂነትና የጋራ አመራር ዘይቤ ነግሶ የሚታይባት ኢትዮጵያን ለመመስረት በአንድነት እንነሣ።
ስልጣን የሕዝብ ነው!! አንድነት ሀይል ነው!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!! ሕዝባችን ያቸንፋል!!
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment