ነሃሴ ፫(ሦስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች እንዳመለከቱት በ ኢድ አል ፈጥር እለት የፌደራል ፖሊሶች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የወሰዱትን እርምጃ ተከትሎ ሌሊቱንና ዛሬም በርካታ ሙስሊሞች ከቤታቸው እየተወሰዱ ታስረዋል።
በአሁኑ ጊዜ በትክክል የታሰረውን ህዝብ ቁጥር ለማወቅ ባይቻልም በሺዎች እንደሚቆጠር ይገልጻሉ። በዛሬው እለትም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእስር ተፈተዋል። ድምጻችን ይሰማ እንደገለጸው ደግሞ በትናንትናው ተቃውሞ አንዲት ነፍሰጡርን ጨምሮ 5 ሰዎች ተገድለዋል። ኢሳት የማቾቹን ቁጥር በትክክል ለማወቅ ጥረት ቢያድርግም አልተሳካለትም፤ አንዳንድ ሙስሊሞች በሚደርስባቸው ከፍተኛ ችግር እየተማረሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራም አልተሳካም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የሙስሊሙን ጥያቄ በኃይል ለመፍታት መሞከሩ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የእምነት ነፃነት ስለጠየቁ የታሰሩ ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱና ተጠያቂዎች ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል።
ሁለት ዓመት ለመሙላት ጥቂት ወራት የቀረውን የሙስሊም ሠላማዊ የመብት ጥያቄ እንዲያከብር፣ መንግሥት በእምነት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆምና ያነሷቸውን ጥያቄዎች በአስተውሎት በማየት እንዲሁም ወደ ውይይት በመምጣት ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መንገድ ምላሽ እንዲሰጥ ፓርቲው ሲያሳስብ መቆየቱን አስታውሷል።
መንግሥት የህዝብ ጥያቄዎችን በኃይል ለመፍታት የሚወስደው ርምጃ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ባሻገርም በህግ የሚያስጠይቀው ተግባር መሆኑን የገለጸው ፓርቲው፣ ከዚህ በፊት ሲጠቀምባቸው የነበሩት የመፈረጅ፣ ሽብርተኛ እያሉ የማሰር፣ የማዋከብና የመግደል ስትራቴጂዎች ህዝቡ መብቱን ለመጠየቅ ወደ ኋላ እንዲል የሚያደርጉት አይደሉም ብሎአል፡፡
አንድነት ” መንግሥት ፊት ለፊት የቀረቡ ጥያቄዎችን መመለስ አለመቻሉ ሳያንስ እንደገና ወደ ኃይል ርምጃ መመለሱ ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል፣ አስተውሎት የጎደለው አካሄድ እንደሆነ ገልጾ፣ አሁንም ከዜጎች እየቀረቡ ያሉ የመብትና የነፃነት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ” ጥሪ አቅርቧል።
በተመሳሳይ ዜናም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የወሰዱትን እርምጃ በጥብቅ አውግዟል።
Posted Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment