August 16, 2013
ነሐሴ 10 ቀን 2005 ዓ.ም
እንደተለመደው የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በመረጃና ደህንነት አገልግሎት ተሰናዳ ያለውን ‹‹ሸህ ኑሩን ማን ገደላቸው?›› በሚል ርዕስ ዶክመንተሪ አዘጋጅቶ አስተላልፏል፡፡ ይህ ዶክመንተሪ የገዥውን ፓርቲ ብፅእና ከመተረክም በላይ ጉልበተኝነትንና ፍረጃን ማእከል አድርጎ ከአኬልዳማ እና ከጃሀዳዊ ሀረካት የቀጠለ በፓርቲያችን እና በዜጎች ላይ የተቃጣ ህገ ወጥ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው፡፡ የመንግስትነት ስልጣን የያዘ አካል ሀገራዊ ችግሮችን ለምን በዶክመንተሪ ፊልም ለመፍታትና ለማዳፈን እንደሚጥር እንቆቅልሽ ቢሆንብንም አሁንም ከዜጎች የሚነሱ ሰላማዊና ህጋዊ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንዳለባቸው ፓርቲያችን በፅኑ ያምናል፡፡ የሙስሊም ወገኖቻችን ጥያቄም በውይይትና በመግባባት ላይ ተመስርቶ ሊመለስ እንደሚገባና የሀይል እርምጃው መቆም እንዳለበት ያለንን ጽኑ እምነትና አቋም ደግመን እናረጋግጣለን፡፡
መንግስት ህዝቡን በዶክመንተሪ ፊልም በማስፈራራት ለማሳመን ከመድከም ባሻገር ዴሞክራሲያዊ ባህሪን መላበስ አልተቻለውም፡፡ ዶክመንታሪ ፊልሙም እንደተለመደው የኢህአዴግ የፍረጃ ፖለቲካ የተንፀባረቀበት፤ የተለየ ሀሳብና ጥያቄ ያቀረቡ ግለሰቦችንና ተቋማትን ማሸማቀቅ ብሎም የማጥፋት እኩይ ተግባር ማሳያ ነው፡፡ ይሄ የጉልበት አካሄድ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ረገጣውን አባብሶ ከመቀጠል ውጭ መፍትሄ የማያመጣ ሲሆን የፓርቲያችንን ሰላማዊ ትግልም ሊቀለብሰው አይችልም፡፡ በተደጋጋሚ እንደገለፅነውም ፍርድ ቤት በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ አድርጎ ውሳኔ ሳያሳልፍ በቴሌቪዥን ፍርድ መስጠቱ ገዢው ፓርቲ በህግ የማይገዛ አምባገነን ስለመሆኑ ግልጽ ማሳያ ሲሆን የፍትህ ስርዓቱ ልዕልናም በአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተገፏል፡፡
‹‹ሼህ ኑሩን ማን ገደላቸው?›› በሚል ርዕስ የቀረበው ፊልም በህጋዊ መንገድ ተቋቁሞ በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን የፓርቲያችንን ስም ለማጥፋት፤ ለመፈረጅና በህዝቡ ዘንድ እየገነባን ያለነውን ተቀባይነት ለመሸርሸር ሆን ተብሎ የተከናወነ የፈራጁን አካል ህገ-ወጥነትም ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ የሙስሊም ወንድሞቻችንን ለሁለት ዓመት የዘለቀ ጥያቄና የሼህ ኑሩን ግድያ ከፓርቲያችን ጋር በማያያዝ ፖለቲካዊ ጥያቄ ለማስመሰል መሞከር ጥፋትም ወንጀልም ነው፡፡
ፓርቲያችን አንድነት አሁንም ዘር፣ ፆታ፣ ሀይማኖት፣ ቀለም ሳይለይ ዜጎች የሚያነሱት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ፤ የመንግስት በሐይማኖት ጣልቃ ገብነትም እንዲቆም ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያረጋግጣል፡፡ የኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት የፓርቲያችን አመራሮች በየግዜው የሚያደርጉትን ንግግሮች ሞያንና ንጹህ ህሊናን በሚያጎድፍ መልኩ እየቆራረጠ ሙሉ ትርጉሙን እንዳይዝ አድርጎ በማስተላለፍ እየፈጸመ ያለው አሳፋሪ ተግባር እንዲታረም ተቋሙን እናሳስባለን፡፡ በሼህ ኑሩ ላይ የተፈጸመው ግድያ በየትኛውም አካል የተፈጸመ ቢሆንም ህገ ወጥ እና ኢሰባአዊ መሆኑን ፓርቲያችን የሚያምን ሲሆን ድርጊቱም በሀገራችን ህግ እንዲዳኝ በድጋሚ እንጠይቃለን፡፡ መንግስትም በፓርቲያችን ላይ እያደረገ ካለው ፍረጃ እንዲታቀብና ወደ ውይይት እንዲመጣ እንዲሁም ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ያነሱትን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲመልስ በድጋሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ነሐሴ 10 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ
Posted By,Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment