(ዘ-ሐበሻ) በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 3ኛ ዓመት ተማሪ የሆኑ ተማሪዎች ከውጤት አሰጣጥ ጋር ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ሲጮኹ መዋላቸውን የዘ-ሐበሻ የባህርዳር ዘጋቢዎች ከስፍራው ዘግበዋል። እንደ ዘጋቢዎቻችን ገለጻ የ3ኛ ዓመት ተማሪዎቹ ጩኸታቸውን ሲያሰሙ ከዋሉ በኋላ የዩኒቨሲቲው ዲን ዶ/ር ባየልኝ ዳምጤ ሰብስበው ያነጋግሯቸው ቢሆንም፤ ዶ/ሩ ችግሩን ከማብረድ ይልቅ እሳት ለኩሰውበት ሄደዋል ሲሉ ተማሪዎቹ ለዘ-ሐበሻ ዘጋቢ ነግረውታል።
ዶ/ር ባየልኝ ተማሪውን ሰብስበው “በቤታችሁ በነበራችሁበት ጊዜ በቀን 2 ጊዜ የምትበሉ ተማሪዎች እዚህ ዩኒቨሲቲ ውስጥ በቀን 3 ጊዜ እየበላችሁ ጠገባችሁ፤ ይሄ ጥጋብ ነው ስለማርክ አሰጣጥ ጥያቄ ያስነሳችሁ” የሚል አንባገነናዊ ንግግር በመናገራቸው ተማሪው ቁጣውን እንዳሰማ የገለጹት የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች “እኛ በችግረኛ ሃገር ላይ ሆነንና የትምህርት ጥራት በሌለበት መልኩ ያደጉ ሃገራት የትምህርት ፖሊሲ መሞከሪያ አንሆንም” በሚል የ3ኛ ዓመት ተማሪዎቹ ቁጣቸውን ገልጸዋል ብለዋል። ይህን ተከትሎም ጉዳዩ እኛንም ይመለከተናል በሚል የባርዳር ዩኒቨርሲቲ 1ኛ እና 2ኛ ዓመት ተማሪዎች የ3ኛ ዓመት ተማሪዎቹን ጥያቄ መቀላቀላቸው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ዘ-ሐበሻ ወደ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ዲን ቢሮ ደውላ የነበረ ቢሆንም ዶ/ር ባየልኝ ዳምጤን ማግኘት አልቻለችም። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አሁንም ውጥረቱ እንዳለ የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ገልጸዋል።
Posted By,Dawit Demelash
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/10019
No comments:
Post a Comment