ማክሰኞ ሕዳር 17/2006
ከመንግስታዊው እስልምና መምጣት በኋላ የህዝበ ሙስሊሙን ድምጽ ለማሰማት የመንግስት ዋነኛ ቢሮዎች ድረስ የደረሱት መሪዎቻችን ዛሬ በግፍ እስር እየተጉላሉ ይገኛሉ፡፡ የህዝብን ድምጽ አሻፈረኝ ያለው መንግስት እያደረሰው ያለው ግፍ አሁንም በህዝበ ሙስሊሙ ላይ እንደቀጠለ ነው፡፡ አሁንም መድረሳዎች በመንግስታዊው እስልምና አጫፋሪዎችና የእነሱን ፍላጎት ለማስፈጸም በሚያጅቧቸው ጠመንጃዎች እየተነጠቁ፣ አላህ የሚመለክባቸው መስጂዶች እየተወረሱ ነው፡፡
መስጂዶቻችንን ተራ በተራ እየቀሙና እያስቀሙ ያሉት አካላት አንዳችም ህጋዊ መሰረት ባይኖራቸውም ድርጊታቸውን ግን ቀጥለውበታል፡፡ ሜክሲኮ የሚገኘውና በተለምዶ ጀርመን ግቢ ተብሎ የሚጠራው መስጂድም በመንግስታዊው እስልምና አጋፋሪዎች ሊወሰድ መሆኑን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ሁሉ በደል መሀል ትእግስት አድርጎና ለመንግስት ነገሮችን በጥሞና የማሰቢያ የእፎይታ ጊዜ ሰጥቶ እየጠበቀ ያለው ህዝበ ሙስሊም የሚደረገውን በደል ሁሉ ያያል፤ ተከታታይ በደል ባላሸነፈው ወኔውም በአላህ ፈቃድ እስከመጨረሻው ይታገላል!
ኢትዮጵያዊው ህዝበ ሙስሊም እስካሁን መስዋእትነት ሲከፍልለት የቆየውን ሃይማኖታዊ ነጻነቱን ሳያገኝ ዳግም እንቅልፍ የሚወስደው አይደለም፡፡ ሲማረው ካደገው እስላማዊ ታሪኩ፣ በቅርብም ድምጹን ሊያሰሙ ዋጋ ከከፈሉለት መሪዎቹና ዳኢዎቹም ላመኑበት አላማ መስዋእትነት መክፈልን ወርሷል፡፡ ምንም እንኳን ዛሬ በዚያ በጎ አላማ ስር ያሰለፉን እነዚያ ብርቅዬ መሪዎቻችን በእስር ቢገኙም መንፈሳቸው ግን አልታሰረም፤ አካላቸው እንጂ ስብእናቸው አልተፈተነም፡፡ ይህንንም ነው በመንግስት ቀጥታ ትእዛዝ እንደልብ በሚጠመዘዘው ችሎት ስር ሆነው ህዳር 23 እየተቃረበ ሳለ ደጋግመን የምናስታውሰው፡፡ ቀኑ በቀረበ ቁጥር የከፈሉትን መስዋእትነት፣ ቃል የገቡለትን አላማ አስፈላጊነት ደጋግመን እያስታወስን ታሪክ መዝግቦ የሚያስቀምጠውን አካሄድ እንታዘባለን፡፡ እስካሁን ለመንግስት ነገሮችን በጥሞና ለማሰብ ከሰጠነው ጊዜ አንጻርም በቀጣይ የሚኖረንን የትግል ስልት ካሁኑ ወኔያችንን እያደስን ልንጠብቅ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያዊው ሙስሊም መብቱን ያውቃል፤ ይፈልጋል፤ በሰላማዊ መንገድ ይታገልለታልም – እስከመጨረሻው!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
Posted By.Dawit Demelash
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/9985
No comments:
Post a Comment