Friday, November 8, 2013

በሙኒክ ከተማ ከወያኔ ካድሬዎችና ከሆድ አደሮች ጋር

ትዝብቱከሙኒክ

የተደረገው ተጋድሎ የሰጠን ተመክሮና ቀጣዩ እርምጃችን!
ሙኒክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ኢትዮጵያ ቀመስ ጉዳዮች ላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተደረገባት ከተማ በመሆኗ ከተለያየ አቅጣጫዎች በተለይም የወያኔን ጎራ ያሰጋና   ትኩረት የተጣለባት የጀርመን ከተማ ሆናለች::  ከዚህም በተጨማሪ ነዋሪዉ ኑሮዉን ለማሸነፍ የሚያደረገዉ ትግል የማህበራዊ ግንኙነት ጊዜዉን በጣም የሚሻማበት ከተማም ነች:: እነኚህን ነባራዊ ሁኔታዎችን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመቁጠር ይመስለኛል የወያኔ ካድሬዎች ጥቂት ለሆዳቸዉ ያደሩ ግለሰቦችንና በእድሜ ለጋ የሆኑ ታዳጊዎችን በጥቅማ ጥቅም በመደለል ለተንኮል አላማቸዉ መሳሪያ አድርገዉ ያሰማሩት::
በዉጪዉ  አለም የሚኖረዉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ራሱን በራሱ ለባርነት አሳልፎ ካልሰጠ በስተቀር የወያኔ መንግሥት  እንደ አገር ቤቱ  የማስፈራሪያም ሆነ የማስገደጃ ጉልበት የለዉም! ስለሆነም ነዉ በየሄዱበት አካባቢ ሁሉ ቤተክረስቲያን እንደገባች ዉሻ ማምለጫ ቀዳዳ እየጠፋቸዉ የሚራወጡት::
የወያኔ መንግሥት ይህንን ጠንቅቆ ስለሚያዉቅ ዲያስፖራዉን ለማጥመድ በፖሊሲ ደረጃ የዘረጋቸዉ ሁለት ወጥመዶች የሚከተሉት ናቸው:-
1. በምንኖርባቸዉ አካባቢዎች የምንመሰርታቸዉን የመገናኛ አዉታሮችን ማለትም ኮሚኒቲዎችን፣ የእምነት ተቋማትን፣ እድሮችን፣ የስፓርት እና ለሎች የመዝናኛ ማዘዉተሪያዎችን መቆጣጠር
2. ዜጎችን በደካማ ጎናቸዉ በመግባት አገር ቤት ገብተዉ ቤት እንዲሰሩ እንበስት (Investment) አድርገዉ ሀብትና ንብረት እንዲያፈሩ ካደረጉ በኋላ የገዛ ንብረታቸዉን መያዢያ አድርጉ እንዳይቃወሙት ማድረግ ነዉ :: ዋናው አላማቸዉ እስካሁን መቆጣጠር ያልቻሉትን በውጭ የሚካሄደውን ፀረ ወያኔ ትግል በጥቅማ ጥቅም እና በሌሎችም ደካማ ጎን በመግባት ማዳከምና የስልጣን ዘመንን ለማራዘም መጣር ነው::   
በሙኒክ ኖቬምበር ሁለት ተሞክሮ የከሸፈዉ የቦንድ ሺያጭና 40 60 የቤት ሥራ  አጀንዳ በታዋቂ ሙዚቀኛ አሳጅበዉ የወያኔ ቡችሎች በመርዝ የተለወሰ ማራቸዉን ይዘዉልን ሊያሳስቱን የመጡት ከላይ የገለጽኩትን በዲያስፖራዉ ላይ የተነደፈዉን ፖሊሲ መተግበሪያ ነበር::
ይህ ከፍተኛ ጊዜና ገንዘብ አባክነዉ በኤምባሲ ድጋፍ ለማካሄድ የሞከሩት የሆድ አደሮች ፕሮጄክት የተደናቀፈዉ በቆራጥ ኢትዮጵያዉያን ጥንቃቄ በተሞላ የአንድ ሳምንት ዝግጅትና የሰዓታት ዘመቻ ነበር:: ታላቅ ዉጤትና አመርቂ የኢትዮጵያውያን አንድነት የታየበት በመሆኑ የሚያኮራ ታሪካዊ ስራ ነዉ::
አበዉ ሰተርቱ ከአንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም እንዳሉት ቆራጥ የሆኑ በጀርመን አገር የሚኖሩ  ወገኖቻችን ተሰባስበው ረጅም ርቀት ተጉዘዉ በመምጣትና ከሙኒክ ወገኖቻቸው   ጋር በመተባበር ዝግጅቱንና አዘጋጆችን ድባቅ አደርገዋቸዋል!
ነገር ግን ይህ ደስ የሚል ውጤት የሚያዘናጋ እና ብዙም የሚያዝናና መሆን የለበትም! ምክንያቱም የተሰማራነዉ ለመከላከል እንጂ ለማጥቃት ወይም ጭራሹኑ እንዳይሞከር ለማድረግ አልነበረምና ነዉ:: ስለሆነም ከዚህ ትምህርት በመቅሰም ሥራችን ሁሌም ሰዶ ማሳደድ እንዳይሆን በጁን 2014 በሙኒክ እንዲደረግ የተፈቀደዉ በአዉሮፓ የኢትዮጵያዉያኖች የስፖርት ወድድር እነኚሁ ግለሰቦች ለወያኔ የእጅ መንሺያ ሊያደርጉት  ስለሚችሉ ከወዲሁ ነቅተን መጠበቅና መስመሩን እንዳይስት የማድረግ  ሃላፊነት አለብን::ይህ ሳይደረግ ቀርቶ በኢትዮጵያ አዬር መንገድ በሌላ ድርጅት ወይም ግለሰብ ስፖንሰርነት አከሂደለሁ በሎ ባለሀብት ፍለጋ መሯሯጡ የማያዋጣ አካሄድና ህጋዊነት የሌለው እንደሆነ መገንዘብ ብችሉ መልካም ይመስለኛል:: እነደ አማራጭም የማቀርበዉ ካሁን በፊት ያለ ምንም ችግር ካዘጋጁት ከኑረንበርግ ወጎኖቻችን ልምድ በመዉሰድ ሁሉን ያካተተ እንዲሆን ማደረግን ነዉ::

ከሁሉ በፊት ግልጽ መሆን ያለበት በዚህ ስፖርት ተጫዋቹ ተመልካቹ አስተናጋጁና ተስተናጋጁ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ የመጀመሪያዉ ጥሪዬ እኛ ብቻ ባሌቤት ነን  ብለዉ ለሚሯሯጡ ጥቂት ግለሰቦች ይህንን የተሳሳተ ግምት ትተዉ ዝግጅቱ በተቻለ መጠን ሁሉን ያካተተ እንዲሆን ለማድረግ ጥረቱን ከወዲሁ እንዲጀምሩት ነዉ ::
ሁለተኛዉ ጥሪ ግለሰቦቹ የጀመሩትን የተሳሳተ አካሄድ ለማስተካከል የማይፈልጉ ከሆነ ያገባናል የምንል የሙኒክ ነዋሪ ኢትዮጵያዉያን በግለሰብም ሆነ በድርጅት ደረጃ ብዙ ህጋዊ አማራጮች እንዳሉን አዉቀን በጋራ መክረን መንቀሳቀስ አለብን::
ሰሞኑን ዉርደት ያከናነብናቸዉ የወያኔ ካድሬዎች ይህቺን ጽሑፍ እንዳነበቡ ስፖርትና ፖሌቲካ ምን አገናኘዉ ብለዉ ለቅስቀሳ እንደሚሰማሩ ግልጽ ነዉ ነገር ግን እኔ መልሴ እናንተዉ ናችሁ እንደ እርጎ ዝንብ ሁሉም እየጠለቃችሁ ያስቸገራችሁን ነዉ::
በዚህ አጋጣሚ ጥቂት ታዳጊ ወጣቶች በምንም ሆነ በምን (at any cost) ገንዘብ፣ገንዘብ ብለዉ የሚቅበዘበዙ ስላሉ በሀገር፣ በህዝብ በተለይም ከዘመድ አዝማድ ርቀን በባዕዳን አገር በምንከራተት ኢትዮጵያዉያን ኪሳራ ለወያኔ ገጽ በረከት ይዘዉ እንዲሄዱ የማንፈቅድ መሆናችንን እያስገነዘብኩ ብዙሃኑን ወጣት ማሳሰብ የምወደዉ እነዚህ ጥቂት ራስ ወዳድ ግለሰቦች መሳሪያ አድርገዉ እንዳይጠቀሙባችሁ ጥንቃቄ እንድታደርጉ ነዉ::
በማጠቃለያ ከሰሜን አሜሪካዉ የኢትዮጵያዉያን የስፖርት ኮሚሺን የምንማረዉ ብዙ መልካም ትምህርቶች ስላሉ የአዉሮፓዉ የስፖርት ኮሚሺን በማንም ተጽዕኖ ስር ላለመዉደቅ ሉአላዊነቱን መጠበቅ ስላለበት በሙኒክ የጥቂት ወጣቶች አካሄድ አደገኛና ለኮሚሺኑም አነድነት አሰጊ በመሆኑ ክትትል እንዲያደርግና በሙኒክ የሚደረገዉ ዝግጅት ሁሉን አቀፍ እንዲሆን በማድረጉ የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት እላለሁ:: ከወጣቶቹ በስተጀርባ ሆነዉ ህብረተሰቡን ለመከፋፈል የሚራወጡ ስላሉ ጥረታቸዉን በተለመደዉ ኢትዮጵያዊ አንድነት ማክሸፍ የሁላችንም ሃላፊነትና ግዴታ ነዉ::
ይህ በቀና መንፈስ ያቀረብኩት የግል አስተያዬት ይመለከተኛል ከሚል አካል አፋጣኝ ምላሽ ካላገኘ በሙኒክ የምንገኝ ኢትዮጵያዉያን የጋራ አቋም ሆኖ ወደተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት ማንነቴን ግልጬ እንደምቀርብ ለማረጋገጥ እወዳለሁ :: አሁን ይፋ ያልሆንኩት አንባቢያንም ሆኑ የጉዳዩ ባለቤቶች ነን ባዮች ከመሰረተ ጉዳዩ በላቀ በእኔ ማንነት ላይ እንዳያተኩሩ በማሰብ ነዉ::


ፈጣሪ አምላክ ኢትዮጵያን ይጠብቃት

አንድነታችን ይጠንክር

   Posted BY. Dawit Demelash

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/9110

No comments:

Post a Comment