November 14, 2013 09:31 pm
የብዙ ሺህ ዘመናት የመንግሥትነት ታሪክ የነበራት አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ መንግሥት አልባ አገር ናት ብሎ ደፍሮ መናገር የሚቻልበት ወቅት ላይ ደርሰናል።
ኢትዮጵያ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ፋና ወጊና የበርካታ ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ትግል ማነቃቂያ ምሳሌ ሆና ቆይታለች፤ ህዝቧም ክብር ያለው ነበር። አሁን ባለንበት ዘመን ግን ኢትዮጵያዊነት የሚያሳፍር የኢትዮጵያውያንም ዋጋ ከእንስሳት ይልቅ የወረደበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
በየተሰደድንበት ሁሉ እንገረፋለን፣ እንታሰራለን፣ እንገደላለን፣ ሴቶች እህቶቻችን ይደፈራሉ። ይህ የኢትዮጵያዊያን የቀን ከቀን ሕይወት ነው! ዓይኖቻችን በርካታ ግፎችን ተመልክተዋል! ጆሮዎቻችን ስፍር ቁጥር የሌለውን የወገኖቻችንን የሰቆቃ ድምፅና የድረሱልኝ ጥሪ አድምጠዋል! በጥቅሉ ኢትዮጵያውያን ረክሰናል! ኢትዮጵያዊ መሆን አሳፋሪ ሆኖአል።
ይህችን ጽሁፍ እንድከትብ ያነሳሳኝ ሰሞኑን በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና ኢሰብዓዊ የሆነ ድርጊት ሲሆን ሴቶች እህቶቻችን ከባሎቻቸው ተነጥለው ተወስደው አንዳንዶቹም በሚወዷቸው ቤተሰቦቻቸው ፊት በብዙ የአረብ ጎረምሶች ተደፍረዋል። በዚሁ የተነሳ ህይወታቸው አልፏል፣ ብዙዎች በአደባባይ ደማቸው ፈስሷል፣ በግፍ ተገድለዋል፤ የተረፉትም በአሰቃቂ ሁኔታ ምግብና ውሃ በሌለባቸው ማጎሪያዎች ተወርውረዋል።
የእነዚህ ወገኖቻችን የድረሱልኝ የጣር ጥሪ አዕምሮን ይረብሻል።
ለነገሩ እንዲህ አይነት ነገር ሲከሰት ዜጎቹ ላይ ይህ ጥቃት የደረሰበት አገር መንግስት በደሉን በፈፀመው መንግስት ላይ ጦርነት እስከ ማወጅ የሚያደርስ እርምጃ ሊያስወስድ እንደሚያስችል ግልፅ ነው። አነሰ ቢባል ግን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ርምጃ ሊወሰድ የግድ ነው። ይህ ሁሉ ወግ ግን መንግስት ካለው አገር እንጂ ካልታደለችው ኢትዮጵያችን እንዴት ሊገኝ ይችላል?
ዋነኛዉ የመንግሥት ሃላፊነት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅና የአገርን ሉዐላዊነት ማስከበር መሆኑ ቢሆንም ኢትዮጵያን የሚገዛው ህወሃት መራሹ ቡድን ግን በሁለቱም አይታማም፤ድንበራችንን ለባዕዳን ደግሞ ደጋግሞ በመስጠት የአገር ክህደት ፈፅሞአል። በርካታ ዜጎቻችን ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሎ ለሰቆቃና ለስደት ዳርጎ ከእነርሱ የተቀማውን መሬት አንድ ፓኮ ሲጋራ ሊገዛ በማይችል ዋጋ ለባዕዳን ቸብችቦታል።
የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑት፤ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ በተካሄደው ጦርነት መሳሪያና ገንዘብ ሲያቀብሉና ሲያቀባብሉ የነበሩት ዛሬም የዜጎቻቸውን ከርስ ለመሙላት ከአላሙዲን ጋር በተደረገ ስምምነት (መሞዳሞድ) በብዙ ሺህ ሄክታር የሚገመት መሬት የወሰዱብን እነዚሁ ዛሬ በወገኖቻችን ላይ አሰቃቂ በደልን የሚፈፅሙት የሳዑዲ አረቦች ናቸው። የህወሃት አገዛዝም ከዜጋው ይልቅ ለእነርሱ እየሰገደ ክብራችንን በሙሉ ጠቅልሎ ሸጦታል።
ከዚህ የተነሳ ቢንቁን ቢገድሉን ማን ጠያቂ አለባቸው?
የዚህ ሁሉ ግፍ ተጠቂ የሆነው ህዝብ ስደትን መምረጡ አንድ ነገር ሆኖ፤ የሚሰደደው ደግሞ ወደ እነዚሁ መሬታቸውን ወደወሰዱባቸው አረቦች መሆኑ የእንቆቅልሹ ሌላው ገፅታ ነው።
እነዚህ ወገኖች ሲሰደዱ ስርዓቱ ከስደተኞች ሊያገኝ የሚችለውን ጥቅም ያሰላል እንጂ ስለሚሰደዱ ዜጎች ግድ የሚሰጠው አይደለም። አሁን በሳዑዲ አረቢያም ሆነ በሌሎች የአረብ አገራት የሚሰደዱትን ዜጎች በኤጀንሲ ስም የሚልኩትና የወገኖቻችንን የሽያጭ ዋጋ ለራሳቸው የተቀማጠለ ኑሮ መደጎሚያ የሚያውሉት የህወሃት ባለስልጣን ዘመዶችና የስርዓቱ ታማኞች መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። በሳውዲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና ቤተሰቦቻቸው ሳይቀሩ የዚሁ የሰው ሺያጭ ኢንቨስትመንት ዋነኛ ተዋናዮች መሆናቸው ይነገራል።
ታድያ በሳዑዲ አረቢያ ባሉ ወገኖቻችን ጣርና መከራ በተመለከተ የህወሃት አገዛዝ ጠንካራ አቋም ከመውሰድ ይልቅ የድርጊቱ ሰለባ በሆኑት ወገኖቻችን ቁስል ላይ እንጨት የመስደድ ያህል ችግር እየደረሰባቸው ያሉት ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው በማለት ሲሳለቅ ተደምጧል።
ለመሆኑ ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ቢሆንስ ዜጎች አይደሉምን? ጥፋት ቢኖርስ በህጋዊ መንገድ ሊጠየቁ ይገባል እንጂ እንዲህ አይነት ሰቆቃ እንዲደርስባቸው እንዴት ይፈቀዳል? ህገወጥ የተባሉትንስ ከአገር ቤት እስከ ውጭ ያለውን የሰው ሽያጭ ሰንሰለት የሚያካሂዱት የራሱ የህወሃት ባለሟሎች አይደሉምን? ይህንስ በማለት ከተጠያቂነት ማምለጥ የሚችሉ ይመስላቸዋልን?
አይደለም! ይልቅስ አገሬ ኢትዮጵያ መንግስት አልባ አገር እንደሆነች ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፥ መንግስት በሌለበት ደግሞ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅና የአገርን ሉዓላዊነት ማስከበር በህዝቡ ጫንቃ ላይ ብቻ ይወድቃል።
በመሆኑም በሳዑዲ አረቢያ ያሉ ወገኖቻችንን ሰቆቃ ለማስቆም ኢትዮጵያውያን በተለይ በውጭ የምንኖር ሁሉ በምንገኝበት አገር በሳዑዲ አረቢያ ኢምባሲዎች ፊት የተዘጋጁ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በመገኘት በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ግፍና ግድያ ባስቸኳይ እንዲቆምና ይህ ካልሆነ ግን ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው እናስገንዝባቸው።
ህወሃት ገና ከጅምሩ በነጻ አውጪ ስም አገር መምራት ሲጀምር ኢትዮጵያን እንደ አገር በመቁጠር ሳይሆን ሕገወጥነትን እና የመሣሪያ የበላይነትን በገሃድ በማሳየት ለመሆኑ የዛሬ 22ዓመት በየአደባባዩ የተረሸኑ ኢትዮጵያውያን ደም ህያው ምስክር ነው፡፡
ስለሆነም ሁለተኛውና ዋነኛው ጉዳይ ለዚህ ሁሉ ስደትና ውርደት ግድያና ሰቆቃ የዳረገንን የህወሃት አገዛዝ እና አስተሳሰቡን ጭምር ነቅለን መንግስት አልባ የሆነችውን አገራችንን የህዝብ መንግስት ባለቤት ለማድረግ የሚካሄደውን ዕልህ አስጨራሽ ትግል በመቀላቀል የድርሻችንን እንወጣ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment