Monday, November 11, 2013

ኢሕአፓ: አርባ አንደኛ ዓመት በዓላችንን ስናከብር

ፓርቲያችን ኢሕአፓ የተመሠረተበትን አርባ አንደኛ ዓመት ለማክበር አባላቱና የፓርቲ ደጋፊዎች በከፍትኛ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ለመገንዘብ ችለናል፡፡ በዓሉ የሚከበርበት ቀን ህዳር 10 ቀን 2006 ወይም ኖቬምበር 23 ቀን 2013 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ እንዲሆን መወሰኑንም ተረድተናል፡፡ ያካባቢው ነዋሪዎች የፓርቲው ወዳጆች እና ደጋፊዎች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዊያን የበአሉ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ በአክብሮት እንደተጋበዙም ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያውያኑ በበዓሉ መገኘት ለበዓሉ ድምቀት ከመስጠትም ባሻገር፤ በዓሉ ከአንድ የፓርቲ በዓል አከባበር አልፎ ተርፎ የኢትዮጵያም በዓል እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ኢሕአፓ የተመሠረተበት ዓይነተኛ ዓላማና ግብ የኢትይጵያን ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ አንድነት ጠብቆ ለማስጠበቅ በመሆኑ፡፡

ይህንን ዓላማና ግብ ርዕይ አድርጎ የተመሠረተ ፓርቲ፤ ላለፉት አርባ አንድ የትግል ዓመታት የዘለቀው፣ ከባድና እልህ አስጨራሽ ትግል እያደረገ መሆኑን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማስገንዘብ አያሻውም፡፡ ምክንያቱም የፓርቲ አባላት የሕዝብ ህይወት ህይወታቸው ፤ችግሩ ችግራቸው፤ በደሉ በደላቸው፤ ጥቃቱና ቁጭቱ ቁጭታቸው፤ ተስፋና ራዕዩም ራዕያቸው በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ዕውነታ ኢሕአፓን ለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ብቻ እንዲያስብና እንዲትከነከን አድርጎታል፡፡ ለኢትዮጵያ መቆምና ለኢትዮጵያ እየታገለ መሰዋቱ ከኢትዮጵያዊነት የተለየ ማንነት፤ ተግባርና ምግባር የሌለው መሆኑ አረጋግጦለታል፡፡ የፓርቲው ራዕይ ዓልፋና ኦሜጋ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ብቻ ነው፡፡

ይህንን ከባድ ሀላፊነት እና ግዴታን የሚጠይቅ ትግል ሲያካሂድ ተዘርዝሮ የማያልቅ ጥቃትና በደል ተደራርቦበታል፡፡ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ጥቅም ስለታገለም የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ባላንጣዎች ተረባርበውበታል፡፡ ባዕዳን ሀይሎችና ሀገር በቀል አጥፊዎች በአንድነት ተሰልፈውበታል፡፡ ሁሉንም እንደየአመጣጣቸው እየተፋለመ ተቋቁሟቸዋል፡፡ ይህንን የመቋቋም ሀይልና ብርታት ያገኘውም ከአይበገሬው ኢትዮጵያዊ ሰብዕናውና ባህሪው ነው፡፡ ይህ የማንነት ባህርይው ደግሞ የድርጅት ነጻነቱን ጠብቆ እንዲታገል አስችሎታል፡፡ ይህ የድርጅት ነጻነትን መስከበር ማለት ደግሞ፣ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ነጻነትና ክብር በቀናኢነት መጠበቅና ማስከበር ማለት ነው፡፡ የዚህ ሀቅ ድምር ውጤት ኢሕአፓ የውጭ ሀይሎችን ርዳታና ድጋፍ እንዳያገኘ አድርጎታል፡፡ የዚህ አይነት እርዳታ ባለማግኘቱ ግን አይቆጭም፡፡ ይህም ሲባል ፓርቲው ትብብርና አይዞህ ባይ አያስፈልገውም ማለት ሳይሆን ርዳታውና ትብብሩ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ጥቅም ላይ የማይደራደር መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል ለማለት ነው፡፡ የቆመበትን ዓላማና ራዕይ የሚፈታተን ማንኛውምን ርዳታና ትብብር ሁሉ ለመቀበል ያልተዘጋጀ ፓርቲ በመሆኑ ጅርጅታዊ ነጻነቱን አስጠብቆ ይታገላል፡፡ በዚህ ጠንካራ መርህ ላይ የተመሠረተ አቋም በመያዙ ብቻ ባላንጣዎቹ እና የኢትዮጵያ ጠላቶች አይንህን ላፈር ይሉታል፡፡ ለእኔ ያልሆነች ኢትዮጵያ ትበጣጠስ ከሚሉት አጥፊዎች ጋር የሞት ሽረት ትግል ሲያካሂድ የኖረውና አሁንም ቢሆን ባይበገሬነት የሚታገላቸው በዚህ ዘመንና ህኔታ በማይለወጠው ጠንካራ አቋሙ ነው፡፡ ይህም ኢሕአፓን ኢሕአፓ ከሚያደርገው ማንነቱ ጋር ሲዳመር ከፍተኛውን የሞራል ልዕልና እንዲኖረው አድርጎታል፡፡

የመንግሥት ሥልጣን አያያዝና አካሄድ የሚመሰረተው፣ መጀመሪያ የዴሞክራሲ ሥርዓት በሀገሪቱ ሲሰፍን ብቻ ነው ብሎ ስለሚያምን እና ለዚህም ስለሚታገል፣ሥልጣንን ባቋርጭ ለመያዝ ሲቋምጡ ከነበሩት እና አሁንም ከሚቋምጡት ጋር የማይስማማው ዋናው ልዮነት ይህ በመሆኑ ነው፡፡ ላለፉት አርባ አንድ ዓመታት የትግል ታሪኩ እንደሚመሰከርለት፣ ሦስቱንም ተፈራራቂ አምባገነን ሥርዓቶች አጥብቆ የተፋለማቸው ዓላማው ይህ ስለሆነ እንጂ ሌላ አብነት ኖሮት አይደለም፡፡ በአንድ የዘመን ቀመር ሲሰላ፣ አርባ አንድ ዓመት የአንድ ትውልድ ዕድሜ ነው፡፡ ቀላል ዘመንም እንዳልሆነ ፓርቲው ይገነዘባል፡፡ በዚህ የትግል ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ካምባገነን ሥርዓቶች ባለመላቀቁ ፣ ፓርቲው እንደ እግር እሳት ያንገበግበዋል፤ ይቆጨዋል፡፡ ይህም በበለጠ ተጠናክሮ ትግሉን እንዲቀጥል አስችሎታል እንጂ ታከተኘ ደከመኘ ብሎ አይቦዝንም፡፡ ይህንን አይበገሬነት እንኳንስ የሚታገልለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀርቶ ባላንጣዎቹም ቢሆኑ ሳይወዱ በግድ በሚገባ ይረዱታል፡፡ እንደ ብረት ቆሎ የማይቆረጠመው በህርይው መንፈሱን ይበልጥ እያጠነከረ ከመታገል በቀር ሌላ ምርጫ እንደሌለው የሚያውቅ ያውቅለታል፡፡ አርባ አንደኛ በዓሉን ሲያከብርም በትግል ሜዳ የተሰውቱን ሰማዕታት በክብር እያስታወሰ እና የተሰውበትንም ብሔራዊ ዓላማ ጠብቆ ከግቡ ለማድረስ ተጠናክሮ በይበልጥ ትግሉን ለመቀጠል ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳኑን በማደስ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን በነጻነቷ ለዘለዓለም ትኑር!

Posted By.Dawit Demelash

http://newstatements.files.wordpress.com/2013/11/the-41-th-anniversary-celebration.pdf

No comments:

Post a Comment