በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በዋልድባ ገዳም ላይ ለሚገነባው የስኳር ልማት ፕሮጀክት በመጀመሪያ ዙር 1800 አባወራዎች ከቦታቸው መነሳታቸውን አንድ አድርገን የተባለው የመረጃ መረብ ዘገበ። “ለተነሱ አርሶ አደሮቹ 127.5 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ተሰጥቷል፡፡” ያለው ይኸው ድረገጽ ለእነዚህ ተነሺዎች ከወራት በፊት የገጠር ከተማ መልክ በመያዝ በተገነባችው የቆራሪት ከተማ ላይ የማስፈር ስራ ተከናውኗል፡፡” ካለ በኋላ “ለዚች ከተማ ምስረታ ምክንያት ደግሞ በዋልድባ ገዳም ላይ የሚሰራው የስኳር ልማት ፕሮጀክት መሆኑን” ዘግቧል።
የዚህ ፕሮጀክት እሳቤ መነሻው 1991 ዓ.ም ቢሆንም አሁን ላይ ግን ወደ እውነታው እየተቃረበ ያለ ይመስላል ፤ ከዓመት በፊት ብዙ ሲያነጋግር የነበረው ይህ የሥኳር ፕሮጀክት አሁን ላይ የቁርጥ ቀኑ የቀረበ መስሏል ፤ መንግሥት ገዳሙን አልነካሁም በማለት አይኔን ግንባር ያድርገው እያለ ቢምልም መሀላው እውነታው ሊደብቀው አልቻለም፡፡ ገዳማውያኑም የሚደርስባቸው መከራ ከቀን ቀን እየጨመረ መምጣቱ ከቦታው የሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ ፤ ጥቂት የማይባሉት መከራውን በመቋቋም የሚመጣውን ነገር ሁሉ በጸጋ ለመቀበል በአቋማቸው ፀንተው አሁንም ድረስ ያሉ ሲሆን ፤ ጥቂት መነኮሳት ግን የመንግሥትን የአምስት አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከግብ ለማድረስ ቀን ከሌት ከመንግሥት ሹማምንት ጋር ዳገት ሲወጡ ቁልቁለት ሲወርዱ ተስተውሏል፡፡” ብሏል።
የ2005 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥኳር ኮርፖሬሽን ዓመታዊ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ጊዜ መንግሥት በበጀት እጥረት የሰፈራ ፕሮግራሙን በአግባቡ ለማስኬድ እንቅፋት እንደሆነበት ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ማቅረባቸው ይታወሳል፤ ከዚህ በተጨማሪም ቦታው ድረስ በመሄድ ስራውን የሚያከናውን የተማረ የሰው ኃይል እጥረት እና ቦታው ላይ ረዥም ጊዜ አለመቆየት መቻልን ለፕሮጀክቱ መጓተት እንደ ሁለተኛ ምክንያት አቅርበው እንደነበር የጠቀሰው አንድ አድርገን ድረገጽ ከውስጥ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት በአሁኑ ሰዓት ዋልድባ ላይ እየተሰራ ላለው የሥኳር ፕሮጀክት የወራት ዝምታ መንስኤው ባለሙያዎች ቦታው ላይ ይህን ሥራ ለመስራት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሲሆን በተለያዩ ጊዜም ለሥራ ወደ ቦታው ያቀኑ ባለሙያዎች በራሳቸው ፍቃድ ስራውን ያለደመወዝ እየለቀቁ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ብሏል።
posted By.Dawit Demelash
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/10689
No comments:
Post a Comment