Friday, December 20, 2013

በህወሓት/ወያኔ መቃብር ላይ ብቻ ኢትዮጵያ በሰላምና በብልጽግና ትኖራለች!

የኢትዮጵያ ህዝብ ማናቸውም መብቶቹ ተነፍጎ የመኖርና ያለመኖር የህልውና ጥያቄ ላይ እንገኛለን:: የህዝቡ የሰብዓዊ መብቶችበየትኛውም ዓለም በማይገኝ መልኩ ይጨፈለቃል ለዚህ ያበቃን ደግሞ ትልቁ ምክንያት የህወሓት/ወያኔን የወንበዴነት ጭካኔ ለመጋፈጥ ያለመፈለጋችን ወይም የጭካኔያቸውን መጠን የሚቋቋም ትግል ባለመኖሩና መስዋዕትነትን ለመክፈል ባለመቁረጣችን የመጣብን መከራ እንጂ ህወሓት/ወያኔ ምንም ስለሆነ አይደለም::  የተቃራነውን ጎራ የልብ ትርታ የተረዳው ህወሓት/ወያኔ ሲፈልገው ይገድላል፣ያስራል፣ ያዋክባል፣መሬትንና ንብረትን በሠበብ አስባቡ ይነጥቃል፣ ከስራ ያባርራል፣ የትምህርትና ሌሎች መብቶችን ገፎ ለመከራ ይዳርጋል ካልሆነም ከአገር ማሳደድን እንደትልቅ አማራጭ ተያይዞታል::
በኢትዮጵያ የመኖር መብት እንዳለንና አገራችን መሆኑን እያወቀ መብቶቻችንን የነፈገን ህወሓት/ወያኔ በማን አለብኝነት መቀጠላቸውን ይሁን ብለን ተቀብለን እኛም መስማማታችን ለዛሬው የባሰበት ችግር አድርጎናል:: እነሱ አገራችን አይደለችም ብለው በሚበዘብዟት አገር ላይ ተንደላቀው እየኖሩ ኢትዮጵያ አገሬ የሚሏት እየተዋከቡ ለችግርና ለመከራ መዳረጋችን እጅግ ያሳዝናል:: አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ለውጥ ልታመጣ የምትችለው ህወሓት/ወያኔ ይዞት ከተነሳው  አገርን የማጥፋት እኩይ ተግባሩና አስተሳሰቦቹ ጋር ወደመቃብር ሲወርድ ብቻ ነው :: ህዝቡም ጨክኖ ለዚህ እውነት ሲነሳ ብቻ ነው::
ከመቼውም ጊዜያት በላይ ህዝባችንና አገራችን ለከፍተኛ ውርደት የተጋለጥንበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል:: በሃገራችን መኖር አልቻልንም፣ በሃገራችን ጉዳይ ላይ መወሰን አልቻልንም ፣በሃገራችን ላይ የበይ ተመልካች ሆነን እንገኛለን፣ በህወሓት/ወያኔ ቀኝ ገዥነት ህዝባችንና አገራችን ለከፍተኛ ብዝበዛ ተጋልጠናል፣ በከፍተኛ ሁኔታ በታጠቁ የህወሓት/ወያኔ በዝባዞች ቁጥጥር ውስጥ ወድቀናል፣ ከፍተኛ ህዝብ ከረሃብ አልፎ ለከፍተኛ ጠኔ ተጋልጦ ይገኛል፣ ይህ አልበቃ ብሎ የአገሪቷ ህዝብ ወደ ውጭ ወጥቶ እንኳን እንዳይሰራ ለከፍተኛ ውርደት ተዳርጎ ማንም እንደፈለገው የሚያደርገውና ተከላካይ የሌለው በዓለማችን ላይ የሚገኝ ህዝብ ለመሆን በቅተናል::
ህዝቡ በአገር ውስጥ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጦ ማንም እንደፈለግ የሚጫወትበት ህዝብ ከመሆኑም በላይ በየትኛውም ነገሩ ላይ ሃይማኖታዊ ጉዳዮቹን ጨምሮ በፈለገው መልኩ እንዳያከናውን መደረጉ ይታወቃል:: ከዚህም አልፎ ደግሞ የአገሪቷ መሬት በተለያዩ ጊዜያት ለተለይዩ ጎረቤት አገራትና ሃይሎች በመስጠትና በማካለል ትልቅ የታሪክ ውርደት ገጥሞናል:: ኢትዮጵያ መቼም ባልታየ መልኩ ለትልቅ ችግር ተጋልጣለች:: ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ትልቅ መስዋእትነትን የሚጠይቅ ትግል ከፊታችን ተጋርጦብናል ይኸውም በህወሓት መቃብር ላይ አገራችንን እንደገና ለማከም የሚያስገድድ ሁኔታ ገጥሞናል:: የህዝብ መብት ጉዳይ ሲነሳ ግድያ፣እስራትና ሞት ሆኗል እጣችን የአገሪቷን ወሰን ለማስጠበቅ የተወሰደው እርምጃም ምንም ባለመሆኑ ዛሬ ኢትዮጵያ መሬቷንና የግዛት ክልሎቿን እየተነተቀጭ ትገናለች::
በአባቶቻችን ተከብረው የነበሩ ድንበሮችን አሳልፎ ለመስጠት ዛሬ ለሱዳንና ለኤርትራም ጭምር እንደፈለገ የሚደራደረው ህወሓት/ወያኔ ገና ያልጨረሳቸው ኢትዮጵያን የማጥፋት አላማዎቹ አላለቁም እና እንዲሁም ቀደምት ወራሪዎቻችን  የፈለጉትን መሬት አባቶቻችን በትግላቸው ያቆዩትን አገር በባንዳዎች በእጅ አዙር ለማግኘት እየጣሩ መሆኑና ለዚህም ተፈጻሚነት ደግሞ የህወሓት/ወያኔ የባንዳ ቡድን ሃላፊነት ወስዶ እየሰራ መሆኑን ስንመለከት ያሳዝናል::
የእነዚህ ባንዳዎች አስተሳሰባቸው እና ድርጊታቸው በኢትዮጵያ ላይ መቀጠሉ እንዲያበቃ ዛሬ በህብረት ብለን መነሳት ካልቻልን ተግባራቸውም ከመፈጸም ሊያቆሙ የሚችሉ አይደሉም :: ህወሓት/ወያኔን ለማሸነፍ ሰዎች የተለያዩ የትግል አማራጮች አዋጭ ናቸው ብለው ባሰቡበት መንገድ ሊሄዱ ይችላሉ፣ ይሁንና አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ግን ህወሓት/ወያኔን በሰላማዊ ትግል እናሸንፋለን ለሚሉ ትግሉ ተገቢ ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ ትግሉን ማቀጣጠልና በአጭር ጊዜ ወደውጤት እንዲመጣ ማድረግ ወይም ትግሉን ትቶ መውጣት ሌላኛው አማራጭ ይሆናል :: ምክንያቱም ህወሓት/ወያኔ በናንተ ስም የኢትዮጵያን ህዝብ እያታለለና ብልጭ ድርግም በሚለው የሰላማዊ ትግል ውስጥ አማራጭ እየመሰላችሁ እየገባችሁ የህዝቡን ተስፋ ሟሟጠጥና ከትግል ማራቅ በፍጹም አዋጭ የትግል ሥልት እንዳልሆነ ሁላችንንም እንረዳለን ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ ህወሓት/ወያኔ በአገሪቷ ታሪክ ውስጥ የፈጠራቸው ዘርን ከማጥፋት ጀምሮ እስከግለሰቦችና ቡድኖች ጭምር ለወሰዳቸው ግፎች  የሚፈለግ ቡድን ከመሆኑም በላይ በትግራይ ህዝብ ሳይቀር በተለያዩ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚፈለጉ ሰዎች ስብስብ በመሆኑ ሰላማዊ ሽግግርን ይፈልጋሉ ብሎ ማሰብ በፍጹም የሚታሰብ አይደለምና ነው::
ለዚህም ምስክር ይሆን ዘንድ በቅርቡ በራያ በተደረገው ስብሰባ ለአቶ አብርሃ አንድ ተሰብሳቢ ያቀረቡላቸውን ጥያቄ መስማት ብቻ ይበቃል እሱም ህወሃት የሽፍታ ቡድን መሆኑን እና ከእነሱ የሚያላቅቋቸው መሆኑን በጥያቄ መልክ ማቅረባቸውንሽፍታማለት ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ የሚታወቅ በመሆኑ ነው::

ይህ ብቻ አይደለም በተለያዩ ጊዜያት አገርን በመክዳትና የአገሪቷንና የህዝቦቿን ጥቅሞች አሳልፎ በመስጠትም የሚፈለጉ ከመሆናቸውም በላይ በሠብዓዊ መብት ረገጣ በኩል አሁን ህወሓት/ወያኔን የሚመሩ ሃይሎች በአገራችን ውስጥ የተፈጸሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን በማቀድ፣ በመተግበርና በማስተግበር በከፍተኛ ሁኔታ በአገር ውስጥና በውጭ ሃገራት የህግ አካላት እንደሚፈለጉ ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆናቸውም ጭምር ነው::
ስለሆነም ይህ ችግራቸው ሊያመጣባቸው የሚችለውን አደጋ በማየት አገሪቷን ለመከላከል ሳይሆን ይህንን የራሳቸውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችላቸውን ሁሉ ለማድረግ እንደቆረጡና ይህንን ችግራቸውን ሊያቃልልላቸው የሚችልን ካልሆነም ጊዜ ሊያራዝምላቸው የሚችልን ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል ማናቸውንም የአገሪቷን ጥቅሞች አሳልፈው ለመስጠት መቁረጣቸውን በቀላሉ መረዳት እንችላለን፣ በምንም መለኪያ ኢትዮጵያዊ እንዳልሆኑ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ከሚወስዱት አረመኔያዊ እርምጃ ልንመለከታቸው እንችላለን::

ከሁሉም በላይ ህወሓት/ወያኔ በተለያዩ ሰዓት የሚቀብራቸው በአንድ ወቅትና ወይም በተለያዩ ጊዜያት ሊፈነዱ የሚችሉ እምቅ ችግሮች በአገራችን ህዝቦች መካከል የፈጠራቸው እንዳሉ ሆነው አሁን ደግሞ ከጎረቤት አገራት በተለይም ከሱዳን ጋር ድንበር ለማካለል በሚል በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር ተጠንሥሶ የነበረውና አብሮት ያልተቀበረው አስተሳሰቡ ዛሬ በቀሪዎቹ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሊተገበር ከፍ ዝቅ እያሉ ያሉበት ጊዜ በመሆኑና በሌላ በኩል ከህወሓት/ወያኔ ማንነትና ይዞት ከተነሳው ዓላማው አንጻር ህወሓት/ወያኔ ሲፈልግ ኢትዮጵያዊ ይሆናል ሳይፈልግ ደግሞ ታላቋ ትግራይ ይሆናል  ስለሆነም ለመሆኑ የማንን መሬት ነው ህወሓት/ወያኔ የሚደራደርበት ? ህዝቦች ለተወሰነ ጊዜ ሊጨቆኑ ይችሉ ይሆናል ሁል ግዜ ግን እየተጨቆኑ ይኖራሉ ማለት ግን እንዳልሆነ አውቆ መረዳት ያልፈለገው ህወሓት/ወያኔ እራሱ ላይ ትልቅ ችግርን ሊያመጣ መቃረቡን በትክክል መገመት ይቻላል::
ህወሓት/ወያኔ በምንም መለኪያ ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነና ኢትዮጵያዊነት ምኑም እንዳልሆነ የራሱ ታሪክ ያሳየናል:: ለዚህም ማስረጃ ለታላቋ ትግራይ ሲሆን አሰብ ይካለላል ለኢትዮጵያ ሲሆን አሰብ የኤርትራ ይሆናል ለህወሓት/ወያኔ ሲሆን ህገመንግስት ይጣሳል ለህዝብ ጥቅም ሲሆን ይኸው ህገመንግስት እንደፈለገ ይተረጎማል፣ የኢትዮጵያውያን ደም በሳውዲ ሲፈስ ህገወጥ ያሰኛል ለዚሁ ሰብዓዊ ግፍ ካሳን ከሳውዲ መጥየቅ ሲግባ 360 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት እቅዶች ለሳውዲዎች ያሸልማል፣ በኢትዮጵያ ላይ የመበታተን አደጋ ስትፈጥር የነበረችው ሱዳን በአምላክ እጅ መልሷን አግኝታ ስትበታተንና ደረቅ መሬቷን ስትታቀፍ ለህወሓት በታታኝ ቡድን ላደረገችው አስተዋጾ 1200 . በላይ በሚሸፍን መሬት ላይ እስከ 50 . ወደ ውስጥ የሚገባን መሬት ለመስጠት ሲሆን ሽንጡን ገትሮ ህወሓት/ወያኔ ሲንቀሳቀስ ምን ይባላል ? ህዝብን የሚያሸብርና ሽብርተኛ እራሱ ህወሓት/ወያኔ ሆኖ ሳለ የህዝብ ወገኖች የሆኑ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ታጋዮች ምንም ትጥቅ ሳይኖራቸው በሽብርተኝነት እየተፈረጁ በየዕስር ቤቶች የሚንገላቱ ለመሆን በቅተዋል::
በአጠቃላይ ህወሓት/ወያኔ የኢትዮጵያዊነት መለኪያም ሆነ ተግባር የሌላቸው ህይሎች ስብስብ የሆነና በኢትዮጵያውያን ደምና ላብ የራሳቸውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ጥማት ለማርካት በቋመጡ  ሃይሎች የተዋቀረ ቡድን በመሆኑና ይህንን የማፍያ ቡድንን እኩይ ተግባርን ለማገዝ በነዚሁ ዘረኞች በተዋቀረ ሠራዊት እየታገዙ አገራችንን ይዘው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠናልና አገራችንን ለማዳን መቁረጥ ይኖርብናል:: ማንም ሊረዳን አይችልም ትግላችን ወደፊት ሲገፋ ግን ብዙዎች አቋማቸውን አስተካከለው ከኢትዮጵያውያን ጋር ይወግናሉ:: ምክንያቱም አገራችን በህወሓት/ወያኔዎች የባንዳ ሃይሎች ብቻ ሳይሆን በታሪካዊ ጠላቶችችንም እጅ ስር በመውደቃችንም ጭምር ነውና ::
ህወሓት/ወያኔ በወልቃይት ጥገዴ ህዝብ ላይ የፈጸመው የዘር ማጥፋት ዘመቻ በሰላም የተጠናቀቀ መስሎት ከሆነ ተሳስቷል:: የወልቃይት ጠግዴ ህዝብ፣ የሲዳሞ ህዝብ፣ የጋምቤላ ህዝብም ሆነ ሌሎች የህወሓት/ወያኔ የጅምላ ጭፍጨፋ ተጠቂዎች ሁሉ እንዳልተሸነፉ መታወቅ ይኖርበታል በእርግጥ መከራቸው ሁሌም የሚያደማ ቢሆንም :: ይልቁንም ህወሓት/ወያኔ አሁንም ሆነ ለወደፊትም ቢሆን በህዝብና በታሪክ ፊት በፍርድ ፊት ሊሆን የቀረበበት ጊዜ ነው:: ህወሓት/ወያኔ የሚቀብራቸው ፈንጂዎች ምን አልባትም በመጀመሪያ የሚያጠፉት እራሱን ህወሓትን/ወያኔን እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ:: ምክንያቱም ለህዝቦች መከፋፈልና እልቂት የቀበራቸው ፈንጂዎች አቅጣጫቸውን ወደ እራሱ  ወደ ህወሓት/ወያኔ እያደረጉ በመሆኑም ጭምር ነው:: ህወሓት/ወያኔና ባለሟሎቹ የኢህአዴግን ስም ተከናንበውና ተሸፋፍነው በህዝብ ላይ የሚፈጽሙትን ደባ ለማስቆም በሚደረገው ትግል ውስጥ ተሳትፎአችንን እናጠናክር በህወሓት/ወያኔ መቃብርም ላይ አዲሲቷን ኢትዮጵያ በጋራ እንመስርት:: ካልሆነ ህወሓት/ወያኔ አገሪቷን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊበታትናት መቁረጡን ከድርጊቱ መመልከት እንችላለን:: ቸር ይግጠመን::


እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

  Posted By.Dawit Demelash

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/11056

No comments:

Post a Comment