December 16, 2013 06:24 am
ከ300 እስከ 500 ሺህ ብር እየተቀበሉ በሀሰተኛ ሰነድ ታራሚዎችን ከማረሚያ እንዲወጡ አስደርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሶስት የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት የስራ ሀላፊዎችና አምስት ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ተጠርጣሪዎቹ ኦፊሰር ገብረመድህን አረጋ፣ ረዳት ኦፊሰር ኢሳያስ ከበደና ዋርደር ኢብራሂም መሀመድ ሲሆኑ፥ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት የእስረኞች አስተዳደር የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው።
ከእነዚህ የስራ ሃላፊዎች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የተቀሩት ግለሰቦች ደግሞ ፥ በንግድ ስራ ይተዳደር የነበረው አቶ ሰለሞን ገለታ፣ አቶ ብሩክ ሀይሌ፣ ወይዘሪት ሳባ ገብረሚካኤል፣ አቶ ናታን ዘላለምና አቶ ቴዎድሮስ ግደይ ናቸው።
የፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የወንጀል ችሎት ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ማመልከቻ ላይ እንደተመለከተው፥ ከሳባ ገብረሚካኤል ውጪ እነዚህ በንግድ ስራ ይተዳደሩ የነበሩ ግለሰቦች ቀደም ሲል በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸውና በማረሚያ ቤት የእስራት ጊዜያቸውን ጨርሰው የወጡ ናቸው።
እንደ መርማሪው ማመልከቻ ሳባ ገብረሚካኤል በኮምፒውተር ፅሁፍ እያገዘቻቸው፥ በንግድ ስራ የሚተዳደሩት ግለሰቦችም ከፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታራሚዎች ከእስር የሚፈቱበትን ትዕዛዝ በሀሰተኛ መንገድ በማዘጋጀት እንዲሁም በሀሰተኛ ፊርማ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ማህተም በማስመሰል አዘጋጅተዋል።
በማረሚያ ቤት የሚገኙና ቅጣታቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆነ 300 ሺህ ብር ከዚያ በላይ ከሆነ ደግሞ 500 ሺህ ብር እየተቀበሉ ፥ ከ11 በላይ ታራሚዎችን በዚህ ሀሰተኛ ሰነድ ከእስር እንዲለቀቁ አድርገዋል ይላል።
የሚያገኙትንም ገንዘብ ለኦፊሰር ገብረመድህን አረጋ፣ ረዳት ኦፊሰር ኢሳያስ ከበደና ዋርደር ኢብራሂም መሀመድ ለተባሉት የማረሚያ ቤቱ የስራ ሀላፊዎች በመስጠታቸው ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
በመርማሪው ማመልከቻ መሰረት እነዚህ የስራ ሃላፊዎች የነበሩ ተጠርጣሪዎች የእስር መፍቻ ደብዳቤው በሀሰተኛ መንገድ የተዘጋጀ እንደሆነ እያወቁ ታራሚዎች እንዲፈቱ በማድረጋቸው ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከሶስቱ የስራ ሀላፊዎች ውስጥ ኦፊሰር ገብረመድህን አረጋ ሀሰተኛ የእስር መፍቻ ካቀረበ አንድ ታራሚ 40 ሺህ ብር መቀበሉ ተመልክቷል።
የጊዜ ቀጠሮ ማመልከቻውን የተቀበለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የወንጀል ችሎት ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ቢለቀቁ መረጃ ያጠፋሉ የሚለውን የመርማሪውን ተቃውሞ በመቀበል ፥ ጉዳያቸውን ማረሚያ ሆነው ይከታተሉ ብሏል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment