Wednesday, May 20, 2015

በእነ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ላይ የተመሰረተው ክስ ተሰማ * ‘ኤርትራን ተሻግራችሁ ግንቦት 7ን ልትቀላቀሉ ነበር’ ተብለው ተከሰዋል

‹‹በይልቃል ጌትነት እና በዮናታን ተስፋዬ ላይ መስክር እያሉ ያሰቃዩኛል›› ብርሃኑ ተ/ያሬድ
የፌደራል አቃቤ ህግ በቀን ሚያዝያ 22/2007 ዓ.ም በእነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ላይ የመሰረተው ክስ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ዛሬ ግንቦት 12/2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በንባብ ተሰምቷል፡፡


በብርሃኑ ተ/ያሬድ ስም በተከፈተው የክስ መዝገብ ላይ አራት ሰዎች የተካተቱ ሲሆን፣ እነዚህም 1ኛ ብርሃኑ ተ/ያሬድ፣ 2ኛ እየሩሳሌም ተስፋው፣ 3ኛ ፍቅረማርያም አስማማው እና 4ኛ ደሴ ካህሳይ ናቸው፡፡ የሽብር ክስ የቀረበባቸው እነዚህ ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ (አንቀጽ 32(1)(ሀ) እና የጸረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 7(1)ን በመተላለፍ ወንጀል እንደተከሰሱ የክስ ቻርጁ ያመለክታል፡፡


በክሱ ላይ እንደተመለከተው ተከሳሾች ኤርትራ ውስጥ መቀመጫውን ባደረገውና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ግንቦት ሰባት ስር አባል ሆነው የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ወስነው ከድርጅቱ ጋር ለመቀላቀል የኢትዮጵያንና የኤርትራን ድንበር አቋርጠው ሊሻገሩ ሲሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ በመሆናቸው በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በአባልነት መሳተፍ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ ክሱን ካዳመጡ በኋላ ጠበቃ ማቆምን በተመለከተ ከፍርድ ቤቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሁሉም ተከሳሾች፣ ‹‹ከተያዝን ጊዜ ጀምሮ በደል እየደረሰብን ነው፤ ይህ የብቀላ ስራ ነው ብለን ስለምናምን እና በዚህ ሁኔታ ተከራክረን ፍትህ እናገኛለን ብለን ስለማናምን የግልም ሆነ የመንግስት ጠበቃ አንፈልግም›› ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ጠበቃ አለማቆም መብታቸው እንደሆነ በማውሳት ሀሳባቸውን የሚቀይሩ ከሆነ ጥያቄያቸውን ለመቀበል ዝግጁ ነው ሲል ገልጾዋል፡፡

በሌላ በኩል አንደኛ ተከሳሽ አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ለፍርድ ቤቱ ባሰማው አቤቱታ እንደገለጸው አሁን በሚገኝበት ቂሊንጦ ማቆያ ውስጥ በደል እየደረሰበት ይገኛል፡፡ ‹‹የተከሰስኩበት ወንጀል በክሱ ላይ የተመለከተው ሆኖ እያለ በግድ ቀድሞ እሰራበት በነበረው ሰማያዊ ፓርቲ ጓደኞቼ ላይ በተለይም በፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት እና በህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ላይ የግንቦት ሰባት አባል እንደሆኑ ተደርጎ መስክር እየተባልኩ ስቃይ እየደረሰብኝ ነው›› በማለት አቤቱታውን ያሰማው አቶ ብርሃኑ፣ በተጨማሪም ማንነትን መሰረት ያደረገ ስድብ እንደሚሰደብ፣ ጨለማ ቤት እንደሚታሰር እንዲሁም የተጠየቀውን ካልፈጸመ ወደማዕከላዊ ሊመልሱት እንደሚችሉ እንደሚዝቱበት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡


ፍርድ ቤቱ በበኩሉ አቶ ብርሃኑ አለኝ ያለውን አቤቱታ በጽሑፍ እንዲያቀርብ በማሳሰብ፣ አቤቱታውን አይቶ የሚመለከተው አካል መልስ እንዲሰጥ እንደሚያደርግ ገልጾዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው ለመቀበል ለግንቦት 28/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41499

No comments:

Post a Comment