Friday, May 1, 2015

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ቤት ተበረበረ • የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ለ‹ምርመራ› ተወስዷል

ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ የሽብር ድርጊት ለማውገዝ ጠርቶት በነበረው ሰልፍ ሳይጀመርና ከሰልፉ በኋላ ተይዘው የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ቤት ተበረበረ፡፡ ካሳንቺስ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ትናንት ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ቀርበው የ6 ቀን ቀጠሮ ከተሰጠባቸው በኋላ ምሽት ላይ ቤታቸው መበርበሩንና ንብረቶቻቸው መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

በብርበራው ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በሰላማዊ ሰልፍና በሌሎች አጋጣሚዎች የሚለብሱት የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ የምርጫና ሌሎች ቅስቀሳ ወረቀቶችም ለ‹ምርመራ› ተወስደዋል፡፡

ቤታቸው ለሰዓታት የተበረበረባቸው ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ማስተዋል ፍቃዱ ሲሆኑ ወይንሸት ሞላ የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ ወረቀቶች፣ የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ ሲዲዎች፣ አርማ የሌለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ (በተናጠል አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የሆነ)፣መጽሐፎች እና ሌሎችም ህጋዊ ሰነዶች እንደተወሰዱባት ገልጻለች፡፡ 
ዳንኤል ተስፋዬ የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ በአንድ ላይ ያስጠረዛቸው የፋክትና የአዲስ ጉዳይ እትሞች፣ ሲዲዎችና ካሴቶች ተወስደውበታል፡፡ በተመሳሳይ ኤርሚያስ ጸጋዬ ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተር፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሰነዶች፣ ሲዲዎች፣ ማስታወሻ ደብተሮችና ሌሎችም ህጋዊ ሰነዶች ተወስደውብኛል ብሏል፡፡
 http://satenaw.com/amharic/archives/6644

No comments:

Post a Comment