Sunday, January 20, 2013


የ“ዝም በል ዳያስፖራ” – አዋጅ፦ ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ እምነት

ኤፍሬም እሸቴ/Adebabay
በዚህ ሰሞን መቼም ከእግር ኳስ ውጪ ማውራት በሕማማት ስለ ቁርጥና ጥብስ እንደማውራት ሳይቆጠር አይቀርም። እኔም ብሆን ስለ እግር ኳሱ ማውራቱን መች ጠልቼው። በርግጥ ይኼ ሁሉ ወፈ ሰማይ የስፖርት ተንታኝ በየኤፍ.ኤሙ ሲተችበት በሚውለው የተጫዋቾቻችን ብቃት፣ ጥራት፣ የኳስ ጥበብ፣ የሽልማት ዓይነት፤ የተጋጣሚዎቻችን ሁኔታ፣ የተጫዋቾቻቸው ዝና፣ ማን ከየትና ከየትኛው ክለብ እንደመጣ፣ አሰላለፋቸው እና ከኢትዮጵያ ጋር ሲገጥሙ ሊኖራቸው ስለሚችለው አያያዝ ለመተንተን ሙያውም መረጃውም የለኝም። (“ችሎታ የለኝም” አለማለቴ ይሰመርበት። ማን ይሞታል። መቸም “አልችልም” ማለት ጎጂ ባህል ሆኗል።) ቢያንስ የእንጀራ አገሮቻችን አሜሪካ እና ስዊዲን ስላፈሯቸው እና ለእናት አገራችን ኢትዮጵያ ስላበረከቷቸው ተጫዋቾቻችን መወያየት ይቻላል።ምን ይሆን ሚሰጥሩ ስንጥቅ የሚያረገኝ፡

ኢትዮጵያውያን እንደ ጨው በመላው ዓለም ተበትነዋል። በብዙ ቦታዎች አንድ ትውልድ አልፎ ሁለተኛ ትውልድ ላይ ደርሷል። በቅርብ ከሚገኙት ኬንያና ሱዳን እስከ አረብ አገሮች፣ ከምዕራብ አውሮፓና ስካንዲኔቪያን አገሮች እስከ አሜሪካና አውስትራሊያ ድረስ ብዙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። ከእነርሱ መካከል የአሜሪካ ሜኔሶታው ፉአድ ኢብራሒም እና የስዊዲኑ ዩሱፍ ሳላህ ተገኝተዋል። ፉአድ ኢትዮጵያ ተወልዶ አሜሪካ ያደገ፤ ዩሱፍ ደግሞ እዛው ስዊዲን ተወልዶ እዛው ያደገ እግር ኳስ ተጫዋች ነው። የብዙ ኢትዮጵያውያን የኋላ ማንነት ማሳይ ሊሆኑ የሚችሉ ልጆች ናቸው። አድገውና ለቁም ነገር ደርሰው አገራቸውን ለመወከል መብቃታቸው ደስ ይላል። “አለ ገና፣ ገና፣ አለ ገና” እንላለን።

ጣዕመ-ኢትዮጵያ፣ ባህለ-ኢትዮጵያ በቀዘቀዘባቸው ባህሎች መካከል አድገው በመጨረሻ አገራቸውን ለመወከል መቻላቸው ትልቅ ነገር ነው። ስለ ፉአድ ያነበብኩት አንድ ጽሑፍ ይህ ወጣት ለአሜሪካ እግር ኳስ ቡድን (ከ17 ዓመት በታች እንዲሁም ከ21 ዓመት ላሉት) ቢጫወትም የማታ ማታ ግን አገሩን ለመወከልና የአገሩን ማሊያ ለመልበስ መወሰኑን ያትታል። ስዊዲን እነ ኢብራሒሞቪችን (በአባቱ ቦስንያዊ) እና ታዋቂው ሔንሪክ ላርሰንን (አባቱ ከኬፕቬርዴ ናቸው) የመሳሰሉ ተጫዋቾችን በማሰለፏ እናውቃታለን። ዩሱፍም ተመሳሳይ በሆነ መልክ ተመሳሳይ ዕድል ሊያገኝ እንደሚችል እገምታለኹ። ነገር ግን ያንን ትቶ የአገሩን መለያ ለብሷል።

ዳያስጶራው ለረዥም ዓመታት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወደ አገሩ በመላክ አገሩን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሲደግፍ ቆይቷል። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዳያስጶራው የሚገኘው ገቢ አገሪቱ ከወጪ ንግድ ከምታገኘው በእጅጉ እንደሚበልጥ የዓለም ባንክ ጥናቶች በተደጋጋሚ አሳይተውናል። ከዚህ የቀጥታ ገንዘብ ርዳታ ባሻገር ትውልደ-ኢትዮጵያዊው በአገሪቱ አጠቃላይ ሕይወት ላይ በጎ ሱታፌ ማሳየቱ አገሩን ለሚወድ ወገን ሁሉ ትልቅ ተስፋ ነው። ዩሱፍና ፉአድ ለዚህ መልካም አብነቶች ይሆናሉ።

ዩሱፍና ፉአድ ወደ አገራቸው ሲመለሱ በዚያው መጠን ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ዳያስጶራነት ጎራ እየተቀላቀሉ ነው። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በዋሺንግተን ዲሲ የተደረገ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን/ት ሐኪሞች ማኅበር ስብሰባ ተገልጿል እንደተባለው በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ዶክተሮች ይልቅ በውጪ የሚገኙት ቁጥር ይበልጣል። አዝማሚያውን ስንመለከተው ይኸው የዕውቀትና የአዕምሮ ስደት እንደሚቀጥል እርግጥ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ዋስትና ማጣት እና ፖለቲካዊ ነጻነት አለመኖር ነው። ከኢኮኖሚው በበለጠ ፖለቲካዊ ጫናው ለብዙው ወገናችን መሰደድ ምክንያት ነው የሚለው የብዙዎች እምነት ነው። በፖለቲካዊ ምክንያቶች የተሰደዱት ደግሞ በየወጡበት አገር ባላቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን መንግሥት ዘወትር መክሰስ ቀጥለዋል። በቅርቡም ይቆማል ተብሎ አይጠበቅም። ይህም ፉአድንና ዩሱፍን የመሳሰሉ ትልውደ ኢትዮጵያውያን በየሙያቸው ትውልድ አገራቸውን እንዳያገለግሉ እንቅፋት ይሆናል። በአገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት ገፈፋ ሲሻሻል ዳያስጶራውም ተጠቃሚ ይሆናል። ዳያስጶራውን በጥቅማጥቅም ማባበል መጠነኛ ደጋፊ ያስገኛል፤ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መጠበቅና ሕገ መንግሥቱን ማክበር ግን ሙሉ ድጋፍ ያስገኛል።

ዳያስጶራው በየሚኖርበት አገር የሚተነፍሰው ፖለቲካዊ፣ ኅሊናዊ፣ አካላዊ እና ሰብዓዊ ነጻነት ይኸው ነጻነት በአገሩ እንዲኖር በጎ ምኞት ይቀሰቅስበታል። ስለዚህ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በአገሩ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ይኮንናል፤ ተጽዕኖ ለመፍጠርም የማይወጣው ዳገት የማይወርደው ቁልቁለት የለም። ይህም የተለያየ አመለካከት መፍጠሩ አይቀርም። ዳጳስጶራው “አክራሪ ነው” ከሚለው ጀምሮ “የአገሩን ነባራዊ ሁኔታ የማያውቅ” እንዲሁም “50 ዶላር ልኮ አገር ውስጥ ያለው ወጣት እንዲማገድ ይፈልጋል” ወዘተ ተብሎ ይቀርባል።

ሐሳቡ ቀደም ብሎ በመንግሥት ብቻ ተደጋግሞ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ተርታ ዜጎችም በማኅበራዊ ድረ ገጾቻቸው ሲያስተጋቡት ይስተዋላል። በአጭር አባባል ለማቅረብ “ዳያስጶራ ዝም በል” ወይም “ዝም እንዲል አድርጉት” የሚል አዋጅ የተነገረ ይመስላል።

በመጀመሪያ ደረጃ አንድን ዜጋ ከአገሩ ርቆ በመኖሩ ስለ አገሩ ያለውን ሐሳብ፣ በመንግሥቱ ላይ የሚኖረውን ቅዋሜ እና ለችግሮች የሚኖረውን መፍትሔ ከማቅረብ ሊከለክለው የሚችል ሕግ የለም። ስለ አገርህ ለመናገር በአገርህ መሬት መኖር አለብህ የሚል “የቀበሌ ትእዛዝ” የመሰለ ሐሳብ ውኃ አያነሣም። ነቢዩ ዳዊት ስለ ኢየሩሳሌም ሲናገር “ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” እንዳለው “እመሰ ረሳዕኩኪ ኢትዮጵያ  ለትርስዐኒ  የማንየ፣ ኢትዮጵያ ሆይ ብረሳኝ ቀኜ ትርሳኝ” የሚሉ ኢትዮጵያውያንን ‘እኮ ምን አግብቷችሁ’ ማለት ከስድብ ይልቅ ያማል።

ዛሬ ባንኖርባት ተወልደንባት አድገንባታል፤ ዘር ማንዘሮቻችን ኖረው አልፈውባታል። ክቡር አጥንታቸው ረግፎባታል። በየወቅቱ በሚመጣና በሚሄድ ሥልጣን የአንድ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱ አይገመገምም። ኢትዮጵያዊነትን ማንም ባለሥልጣን አልሰጠንም፣ ማንምም አይነፍገንም። ከደርቡሽና ቱርክ፣ ጣሊያንና ግብጽ፣ ከሌሎችም ድንበር ገፊዎች ሲታገሉ በወደቁ ወገኖቻችን የቆመ ዜግነት እንጂ እንጀራ ፍለጋ፣ ነጻነት ፍለጋ እንደምንኖርባቸው አገሮች በወረቀት ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም። ኢትዮጵያዊ ዜግነት ከወረቀት እና ከፖለቲካ ወገንተኝነት እንዲሁም ከየብሔረሰባዊ ማንነታችን በላይ ነው።

በሌላም በኩል ካየነው ስለ ሰብዓዊ መብት ለመናገር የግድ የዚያ አገር ዜጋ መሆን፣ በዚያ አገር መኖርም አይጠይቅም። ሰብዓዊ መብቱ እንዲጠበቅለት የሚፈልግ ማንም ሰው የሌላው ሰው መብት ሲጣስ አይደሰትም። ሌላው ሁሉ ታሪካዊ ሐተታ እንኳን ቢቀር በቅርቡ ዘመን የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ከኛ ሚሊሻ ጋር አብረው የተዋደቁልንን ኩባውያንን  መስዋዕትነት እንደምናከብረው፣ ዕድሜ ዘመናቸውን በሴቶች (ፊስቱላ) ሕክምና ረገድ አገራችንን የጠቀሙትን ሐኪሞች እንደምናመሰግነው ሁሉ ለዜጎቻችን ሰብዓዊ መብት የሚከራከሩትንም በዚሁ መነጽር ልንመለከታቸው ይገባል።

በተጨማሪም የመንግሥትን አሠራር ማሔስ አገርን መተቸት አይደለም። መንግሥት የአገር መሪ እንጂ አገር አይደለም። ፓርቲና መንግሥትነት ከዘር ጋር በመቆራኘታቸው ፓርቲውን መተቸት የመጣበትን ዘር እንደመውቀስ ተደርጎ መቆጠሩም ትልቅ ስሕተት ነው። ፓርቲዎች በዓላማቸውና በአሠራራቸው መነቀስና መተቸት ግዴታቸው ስለሆነና በዘር ላይ የተመሠረተ የፓርቲ አወቃቀር እስካለ ድረስ ከፓርቲው ጀርባ ያለው ዘር ወቀሳው ለርሱ የተወረወረ አለመሆኑን ለመረዳት ብዙ ጥበብ አያስፈልገውም።

እንኳን የኢትዮጵያ መንግሥት በዲሞክራሲያዊነታቸው ወደር የማይገኝላቸው አገሮች የየጊዜው መንግሥታት ሳይቀሩ ከትችት አያመልጡም። ትችት መንግሥታቱን ከዓምባገነንነት የሚያተርፋቸው ፍቱን መድኃኒት ነው። ተቃዋሚዎችን፣ ፕሬሶችን፣ ጥቃቅን ስብስቦችን ሁሉ በመዋጥና በዓይነ ቁራኛ በመመልከት፣ ትችትን ሳይሆን ተቺውን በማፈን ጥሩ መንግሥት መሆን አይቻልም። “ልማት ላይ ነን አትንኩን” የሚል ፈሊጥ ወንዝ አያሻግርም። ጥያቄው ግድቡና ሕንጻው ላይ አይደለም። የዜጎችን ሰብዓዊ ሕንጻ እያፈረሱ የድንጋይ ሕንጻ እንሠራለን ማለት አይቻልም። ከግዑዝ ሕንጻ ሰብዓዊ ዜጋ ይቀድማል፤ከግድብ ግንባታም መብት ይቀድማል።

በውጪ የሚገኘው ዜጋ የአገሩን ሁኔታ በትኩረት ለመከታተል ቴክኖሎጂው ትልቅ ዕድል ይሰጠዋል። አራት ኪሎ የተፈጠረው አቃቂ፣ አንዱ ክፍለ ሀገር የተሠራው ሌላው ሳይረዳው ሳይሰማ፤ እረኛና አዝማሪ እንኳን ለዘፈኑና እንጉርጉሮው በራሱ ላይ ግላዊ-ሴንሰርሺፕ በጣለበት ዘመን፣ ከአንድ አፍ በሚወጣ ተመሳሳይ፣ ተደጋጋሚና ቁጥጥር የተደረገበት ወሬ አገር በሚተዳደርበት ጊዜ፣ አለመስማትን እና አለማወቅን (መንግሥታዊ የመረጃ ግርዶሽን) መታገል ሲገባ የሰማውንና ያወቀውን “እኮ ማን ስማ አለህ” ማለት አያዋጣም። ይህንን የሚለው አካል ነገሩ እንዳይሰማበት የፈለገው እንጂ ተጎጂው አለመሆኑም በቅጡ ይታወቃል።

ዳያስጶራውን አምርሮ የመጥላት እና በጅምላ ክፉ ስም የመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራ ፍሬ ማፍራቱን ለማወቅ ተርታ ግለሰቦች እና ቤተ እምነቶች ሳይቀር ማንጸባረቅ የጀመሩትን ተመሳሳይ አመለካከት መመልከት ይገባል። የግለሰቦቹን እንኳን ለጊዜው ብናቆየው የአንዳንድ ቤተ እምነት አስተዳደሮችና መሪዎች ከውጪ የሚመጣላቸውን የአማኛቸውን ሐሳብ፣ ልክ እንደ መንግሥት፣ “አፍራሽ፣ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጥያቄ” አድርገው ሲመለከቱት ማየት እየተለመደ መጥቷል። ‘አጋጣሚ ነው ወይስ የተላለፈ አዋጅ አለ?’ የሚያሰኝ ነው። የቤተ እምነት መሪዎች ሰማያዊውን መንግሥት መጠበቅ ትተው ምድራዊውን መንግሥት ለመጠበቅ ደፋ ቀና ሲሉ እነርሱን የሚከተላቸው ምእመን እንደሚመለከታቸው እንኳን ይዘነጉታል። እነርሱም ከምድራዊው ባለ ጉልበት ጋር ተደርበው “ውጪ ያላችሁት ዝም በሉልን፣ እንደፈቀድን እንሁን” ሲሉ አዋጃቸውንም በደህና ጊዜ የሚናገሩትንም ሰማያዊ ቃል የሚሰማቸው ጆሮ ያጣሉ። በርግጠኝነት ግን ማንም ዝም አይልም።

መልካም ዕድል ለብሔራዊ ቡድናችን!!!!

 ይቆየን – ያቆየን

posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment