Thursday, January 31, 2013


ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአራት የሚዲያ ተቋማት ላይ ክሥ መሠረተ

ክሡ ‹‹ሓላፊና ተጠያቂ የሌላቸውን አንዳንድ የመረጃ መረቦች ዋቢ በማድረግ መሠረተቢስ አሉባልታዎችንና የሐሰት ወሬዎችን በማናፈስ የሽግግር ወቅቱ በሰላም እንዳይከናወን ትርምስ መፍጠርና ሕዝብን ማደናገር›› የሚል ነው
‹‹ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀጣይ ጉዞ በማስመልከት ጉባኤዎችን በማድረግ፣ በውስጥም በውጭም ያለውን ተጨባጭ ኹኔታ በመዳሰስና በሐቅ ላይ በመመርኰዝ የ፮ኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የሚካሄድበትን ኹኔታ በማመቻቸት ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡›› /የሕዝብ ግንኙነት መመሪያው ለሚዲያ አካላት ካሰራጨው መረጃ/
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሕዝብ ግንኙነት መመሪያ ‹‹የሽግግር ወቅቱን በተመለከተ በሚመለከተው አካል መግለጫ ያልተሰጠባቸውን ዘገባዎች እንደተሰጡ አድርገው በማውጣት ግልጽ የኾነ መሠረተቢስ አሉባልታ አናፍሰዋል፤ ሕዝብን አድናግረዋል›› ባላቸው አራት የሚዲያ ተቋማት ክሥ መመሥረቱን አስታወቀ፡፡

ክሥ የተመሠረተባቸው አራቱ የሚዲያ ተቋማት አንድ ሳምንታዊ ጋዜጣ እና ሦስት መጽሔቶች ናቸው፡፡ በስም ዝርዝራቸውም፤
የኛ ፕረስ ጋዜጣ – ዮርዳኖስ ሥዩም ሚዲያ ሓላ/የተ/የግ/ማ
ሎሚ መጽሔት – በዳዲሞስ ኢንትርቴይመንትና ፕሬስ ሥራዎች ሓላ/የተ/የግ/ማ
አርሂቡ መጽሔት – ሳንኮፋ ሓ/የተ/የግ/ማኅበር
ሊያ መጽሔት – ሊያ የኅትመት እና ማስታወቂያ ድርጅት የሚዘጋጁ ናቸው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ‹‹የሽግግር ወቅቱን በሰላም ለማሳለፍ ሌት ተቀን ደፋ ቀና›› በማለት ላይ እንዳለ የገለጸው የመምሪያው ደብዳቤ÷ ሕዝብ ክርስቲያኑን ለማደናገር ኾነ ብለው ይንቀሳቀሳሉ ያላቸው ጋዜጠኞች ዓላማ ‹‹በአባቶች መካከል ጸብና ችግር አለ ብሎ አንባቢው እንዲያምንና ቅዱስ ሲኖዶሱን መበታተን›› ነው፡፡ ደብዳቤው አያይዞም እኒህን ጋዜጠኞች ዝም ብሎ መመልከት ‹‹የጥፋታቸው ተባባሪ መኾን ነው፤›› ስለዚህም ‹‹ጉዳያቸውን ወደ ሕግ አካላት ማድረስና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማተራመስ እያደረጉት ላለው እንቅስቃሴ በሕግ አግባብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ የግድ ይኾናል፤›› ብሏል፡፡
በሕዝብ ግንኙነት መመሪያ ሓላፊው አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ኀይለ ማርያም ፊርማ ለሚዲያ አካላት የተሰራጨው ደብዳቤ እንደገለጸው÷ ክሥ የተመሠረተባቸው የግል ሚዲያ ተቋማቱ ‹‹በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም ኾነ በሚመለከታቸው አካላት ማብራሪያና መግለጫ ያልተሰጠበትን›› ዜና የሚያወጡት÷ ‹‹ከልዩ ልዩ የመረጃ መረቦች አግኝተናል›› በሚል ነው፡፡ መመሪያው በስም ለይቶ ያልጠቀሳቸውን ‹አንዳንድ› የመረጃ መረቦች ‹‹ሓላፊና ተጠያቂ የሌላቸው›› ሲል ገልጧቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ስማቸውን ለይቶ ያልዘረዘራቸውንና ‹‹ትክክለኛ መረጃን ለሕዝቡ ለማድረስ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር እውነተኛ ዜና የሚያስተላልፉ›› የግል ሚዲያ ተቋማትን አድንቋል፤ አመስግኗል፡፡
መረጃን ከትክክለኛው ቦታ በማግኘት ሐቁን ለሕዝብ ማስተዋወቅ ተገቢና ትክክለኛ አሠራር መኾኑን የሕዝብ ግንኙነት መመሪያው ያምናል፡፡ ጎልቶ ከሚሰማውና ብርቱ ሕዝባዊ ግፊት ከሚደረግበት የቤተ ክርስቲያናችን የአንድነትና ሰላም ጥያቄ አንጻር ‹‹ሐቅ›› የኾነው ነገር አከራካሪ ቢኾንም ሕዝብን ለማሳወቅ፣ ለማስተማር እና ለማሳመን መሥራት የሚገባቸው ሚዲያዎች ትክክለኛ መረጃን ማድረስ እንደሚገባቸው አያጠያይቅም፡፡
ጥያቄው ግና÷ በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሥር በቅርቡ የተዋቀረውና ስለ ቅ/ሲኖዶሱ ውሎ ይኹን ስለ ጠቅላላ የአስተዳደሩ እንቅስቃሴ መረጃን የመስጠት ግንባር ቀደም ሓላፊነት ያለበት የሕዝብ ግንኙነት መመሪያ በአግባቡ የተደራጀ ነው ወይ? መዋቅራዊ ነጻነት አለው ወይ? መረጃን በተጠየቀ ጊዜ ይኹን በመደበኛ ጊዜ ለመስጠት ብቁ፣ ፍቁድ፣ ድርጁና ዝግጁ ነው ወይ? ከኾነስ ቀጣይነቱን ጠብቆ ቀጥሏል ወይ? የሚሉት ናቸው፡፡
ሌላም ጥያቄ አለ፡፡ በቀናው አስተሳሰብና አሠራር የሚዲያ ጥፋት በሚዲያዊ አሠራርና መንገድ ይታረማል፤ ይቃናል እንጂ በክሥ እና በቅጣት መኾኑ አግባብ ነው ወይ? በተለይም አካሄዷ አስተማሪ እና አርኣያ የኾነችውን ቤተ ክርስቲያናችንን ከሚመራ አስፈጻሚ አካል ክሥንና ቅጣትን ማስቀደም አግባብ ነው ወይ? ከኾነስ የሚዲያ ተቋማቱ መሠረተቢስ የተባለውን መረጃ እንዲያርሙ ትክክለኛው አሠራር ዘርግቶ መረጃውን በመስጠት የሚታረሙበት የትዝብት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል ወይ?
ብዙዎች እንደሚያምኑት፣ አስተዳደራዊ አንድነታችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን ሰላም በሚመለከት በመስቀለኛ መንገድ ላይ በምንገኝበት በአሁኑ ወቅት÷ በጉዳያችን ላይ ትኩረት ሰጥተው ከሚዘግቡት ሚዲያዎች ጋራ በጎ የሥራ ዝምድናን በሚያሻክር ግንኙነት ውስጥ መገኘት ጎጂነቱ ያመዝናል፡፡ የሰላማዊ ሽግግሩን ይኹን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሎን በተመለከተ ስሕተት የታየባቸው፣ እውነቱን ለመናገር ደግሞ ዘረኝነት የተጠናወታቸውና ከሐቅ የራቁ ዘገባዎች አልታዩም አንልም፡፡ ነገር ግን ተስፋ አለን÷ ጠቅ/ቤተ ክህነቱ ሚዲያዊው ስሕተት በሚዲያዊ አሠራር ይታረም ዘንድ በክሥ የጀመረውን መንገድ እንደሚያጤን፡፡
posted by Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment