Monday, January 28, 2013

የኦሮሞ ተወላጆች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጠየቁ

ጥር ፳ (ሀያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኦሮሞ ጥናት ማኅበር፣ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ድርጅት፣ የኦሮሞ ወጣቶች ራስ አገዝ ማኅበር፣ የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግና የኦሮሞ ድጋፍ ቡድን የተዘጋጀው ደማቅ የተቃውሞ ሰልፍ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ኦልባና ሊሌሳን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
የአሜሪካ ድምጽ እንደዘገበው ከአቶ በቀለ ገርባ እና ከአቶ ኦልባና ሌሊሣ በተጨማሪ በስም የተጠቀሱት ወልቤካ ለሚ፣ አደም ቡሣ፣ ሃዋ ዋቆ፣ ሞሐመድ መሉ፣ ደረጀ ከተማ፣ አዲሱ ምክሬ እና ገልገሎ ጉፋ በእሥር ላይ እንደሚገኙ የሠልፉ አስተባባሪዎች ተናግረዋል፡፡x

የኦሮሞ ተወላጆች ሠልፍ በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት
የኢትዮጵያ መንግሥት አቶ በቀለ ገርባን፣ አቶ ኦልባና ሌሊሣን፣ እንዲሁም ሌሎቹንም ሰባት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ በፖለቲካ ምክንያት ተይዘው የረዥም ዓመታት እሥራት የተፈረደባቸውን ሰዎች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕገመንግሥት እንዲያከብር፣ ከፍርድ ውጭ የሆኑ ግድያዎችንና ንፁሃን ሰዎችን ያለክስ ለተራዘመ ጊዜ ማሠሩን እንዲያቆም የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ጫና እንዲያደርግ ጠይቀዋል።


ከዚህ በተጨማሪ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብት ድጋፍ ከመስጠቷ በፊት የፖለቲካ እሥረኞች ሁሉ እንዲፈቱ አስገዳጅ ጫና እንድታደርግ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞን ሕዝብና የሌሎቹንም ሰብዓዊ መብቶች፣ ሃሣብን የመግለፅና የመደራጀት ነፃነቶችን እንዲያከብር አሜሪካ እንድትጠይቅ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት መሠረታዊ የሆኑ የዜጎችን መብቶች የሚጥሱ አዳዲስ ሕግጋትን ሁሉ፣ በተለይ ፀረ-ሽብር የሚባለውን ሕጉን፣ የፕሬስ ሕጉን፣ የረድዔት ድርጅቶች በሃገሪቱ ውስጥ እንደልባቸው እንዳይንቀሣቀሱ የሚገድበውን የሲቪል ማኅበራት ማቋቋሚያ ሕጉን፣ እንዲሁም ስካይፕንና ሌሎችም የሚድያ አገልግሎት ዘዴዎችን መጠቀምን ሕገወጥ የሚያደርገውን በቅርብ ያወጣውን ሕጉን እንዲሠርዝ እንዲሁም መንግሥት የሃይማኖት ነፃነትን እንዲያከብር እና በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ውስጥም ጣልቃ መግባት እንዲያቆም የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እንዲጠይቅ የሚሉ ጥያቄዎች መቅረባቸውን ሬዲዮው ዘግቧል።x

የኦሮሞ ተወላጆች ሠልፍ በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት
ድርጅቶቹ ለኢሳት በላኩት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት ደግሞ የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ላኢ ትርጉም ያለው ጫና ማሳደር ካልቻለ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሞ እና በሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ይቀጥላል።


የኦሮሞ ተወላጅ ለስቴት ዲፓርትመንት በቀጥታ ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በግልባጭ በላኩት ደብዳቤ ላይ አናሳው የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ( ህወሀት) 40 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ በሚወከለው የኦሮሞ ህዝብ ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው ብለዋል።
ደብዳቤው የሬቻን በአል ለማክበር በቢሸፍቱ የተገኙ 200 የኦሮሞ ተወላጆች ላለፉት አራት ወራት መታሰራቸውንና አሁንም አለመፈታታቸውን ጠቅሰዋል። እንዲሁም በየጊዜው ላለፈው አንድ አመት በየሳምንቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እንደሚታሰሩ፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተነሳው የዘር ግጭት 99 ተማሪዎች አብዛኛኦቹ የአሮሞ ተወላኮች መታሰራቸውን አውስተዋል። እንዲሁም የህወሀት አገዛዝ ባለፉት 21 አመታት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው የአሮሞ ተወላጆችን ሲያስር፣ ሲያሰቃይና ሲገድል መቆየቱን ገልጸዋል።
በቃሊቲ እስር ቤት ከታሰሩ እስረኞች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኦሮሞ ተወላጆች መሆናቸውን ከእስር ቤት ፖለቲከኞች መናገራቸው ይታወቃል።
  Posted By Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment