Friday, January 25, 2013

የሙስሊሙ ህብረተሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የክስ መዝገብ በዝግ ችሎት እንዲታይ ተወሰነ

January 25, 2013 6:43 am
427763_518431121521635_559887398_n
በእነ አቡበከር አህመድ የክስ መዝገብ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት በመታየት ላይ ያለው ክስ በዝግ ችሎት እንዲታይ ተወሰነ፡፡ ከአራት ጊዜ በላይ ልደታ በሚገኘው ፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ይታይ የነበረው ጉዳይ በትላንትናው ዕለት ችሎቱ ወደ አቃቂ ሄዶ ክሱን ተመልክቶታል፡፡ በቀድሞ አጠራር ወረዳ 27 ቀበሌ 08 አዳራሽ ችሎቱ ተሰይሟል፡፡ ጉዳዩን ለመከታተል የተከሳሽ ቤተሰቦች የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች በሥፍራው ተገኝተዋል፡፡
መዝገቡን የያዙት የግራ ዳኛ እንዳሉት “መዝገቡ የተቀጠረው የዐቃቢ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ነው” ካሉ በኋላ “ይሁን እንጂ በቅድሚያ ዐቃቢ ህግ ያቀረበው አቤቱታ አለ፡፡” በማለት ፍ/ቤቱ የደረሰውን የጽሑፍ አቤቱታ ለጠበቆቹ ሰጥተዋል፡፡ ተከላካይ ጠበቆች ጹሑፉን ከተመለከቱ በኋላ ከተከሳሾች ጋር ተነጋግረውበታል፡፡ በመቀጠልም ጠበቆች ለፍ/ቤቱ በሰጡት መልስ “ዐቃቢ ህግ ያቀረበው አቤቱታ መብትን የሚጋፋ፤ የመከራከርን መብት የሚያጠብ ነው፡፡ አሁን በቃል መልስ ለመስጠት እንቸገራለን፡፡ ጉዳዩ ለሌላ ጊዜ ይቀጠርና በጽሑፍ መልስ እንስጥ፡፡” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ዳኞች ከተነጋገሩ በኋላ በሰጡት ትዕዛዝ “ለሌላ ጊዜ ሊቀጠር አይችልም የአንድ ሰዓት ጊዜ እንሰጣችኋለን፡፡ ተነጋግራችሁ በቃል መልስ ሰጡ፡፡” በማለት አዞ ከችሎት ተነስቷል፡፡
ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ ለተሰየመው ችሎት ጠበቆች መልስ ሰጥተዋል፡፡ በሰጡት መልስም “ዐቃቢ ህግ ባቀረበው ጽሁፍ በምስክሮቼ ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ተፈጽሞብኛል ብሎአል፡፡ ማስፈራሪያውና ዛቻው መቼና የት እንደተፈፀመ አልገለፀም፡፡ ምስክሮችን የሚያውቀው ዐቃቢ ህግ ብቻ ነው፡፡ ዐቃቢ ህግ በራሱ ጥፋት ደንበኞቻችንን ሊጠይቅ አይገባም፡፡ አቤቱታው በማስረጃ ተደግፎ አልቀረበም፡፡ ከዚህ በፊት ዐቃቢ ህግ ላቀረበው ክስ በቂ ማስረጃ አላቀረበም፡፡ የሰውም ምስክር የለውም ብለን ስንል፡፡ “ምስክሮቼ አሉ፡፡ ሲቀርቡም ፊታቸውን አንሸፍንም፡፡ ድምፃቸውንም አንቀይርም” ብሎ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ በዝግ ይታይልኝ ብሎአል፡፡ አንድ ክስ በዝግ ሊታይ የሚችለው የህዝብ ሞራል ለመጠበቅ ሲባል የተከራካሪዎችን የግል ህይወትና የአገርን ደህንነት የሚያናጋ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ እስልምና ሃይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ ምስክሩም መስጊድ የሚገባ ሙስሊም መሆን አለበት፡፡ ችሎቱን በዝግ የሚያጠይቅ ጉዳይ የለውም፡፡ ስለዚህ የተከበረው ፍ/ቤት ችሎቱ የአገሪቱ ህገመንግስት በሚፈቅደው መሠረት በግልጽ እንዲከናወን ይወሰንልን፡፡” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡
ዐቃቢ ህግ በሰጠው የመልስ መልስ “ጠበቆች የግል አቋማቸውን መግለጽ አይጠበቅባቸውም፡፡ በህጉ መሠረት የሞያውን ሥነ ምግባር መጠበቅ ይገባቸዋል፡፡ እኛ ያቀረብነው አቤቱታ በማስረጃ የተደገፈ ነው፡፡ ስለዚህ በዝግ ይታይልን፡፡” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የግራና ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍ/ቤት ከሰዓት በኋላ በድጋሚ ከተሰየመ በኋላ በሰጠው ብይን “ክርክሩ በዝግ ችሎት እንዲታይ” ወስኖአል፡፡ በሌላ በኩል ስድስት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በቅርቡ የተቋቋመው መጅሊስና አላማ እንዲፈርስ በፌደራሉ የመ/ጸ/ፍ/ቤት ኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ ችሎት የከፈቱት ክስ ፋይል ተዘግቷል፡፡ ፍ/ቤቱ ፋይሉን የዘጋው ክሱን የማየት መብት የለኝም በማለት ነው፡፡ ባለፈው ሰኞ ጥዋት የተሰየመው 1ኛ የምድብ ችሎት ፋይሉን ዘግቶ ተካራካሪዎች አሰናብቷል፡፡
Posted By  Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment