Tuesday, January 29, 2013

ቤተ ክህነት የፓትርያርክ ምርጫን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱትን አስጠነቀቀች

- በአንዳንዶቹ ላይ ክስ መሥርታለች፤

(ሪፖርተር ጋዜጣ)፦ የቀድሞውን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ሕልፈት ተከትሎ፣ ስድስተኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ ሰላማዊ የሽግግር ጊዜውን ለማደናቀፍ የሚገኙ ቡድኖችን፣ የመገናኛ ብዙኅንና ግለሰቦችን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አስጠነቀቀ፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔን በማሟላት የቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና በሚያዘው መሠረት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን በመምራት በሕጉ መሠረት መንበሩን የሚጠብቁ አባት በመሰየም ቀጣይ ጉዞ ሰላማዊ ለማድረግ እየተሠራ ባለበት በአሀኑ ጊዜ፣ ከውስጥና ከውጭ ያሉ በጐ አመለካከት የሌላቸው ግለሰቦች አፍራሽ ተግባር እየፈጸሙ እንደሚገኙ ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡
የስድስተኛውን ፓትርያርክ አሿሿም በሚመለከት ሕገ ደንብ ወጥቶ ምርጫውን ተግባራዊ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ውስጥ መሆኑን የሚያውቁ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኅን፣ ከውስጥ አፍራሽ ኃይሎች የሚቀበሉትን ፀረ ሰላምና ከእውነት የራቀ አሉባልታ ከድረ ገጽ ያገኙ በማስመሰልና ‹‹ምንጮቻችን›› እያሉ በውጭና በአገር ውስጥ ያለውን ምዕመናን እያወናበዱ በሚገኙት ላይ፣ ቤተ ክህነት ክስ መመሥረቷን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

በአንድነትና በመደማመጥ መንፈስ እየሠራ የሚገኘውን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ አሉባልታ በመንዛት ትርምስ እንዲፈጠር ለማድረግ የሚንቀሳቀሱት ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች ከቃላት ያለፈ ተግባር መፈጸም የማይችሉ ቢሆንም፣ ዝም ብሎ መመልከቱ ድርጊታቸውን እንደመደገፍ ስለሚቆጠር፣ በቀጣይም በመገናኛ ብዙኅኑም ላይ ሆነ በግለሰቦቹ ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ቤተ ክህነት በዝግጅት ላይ መሆኗን፣ የቤተ ክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ አስታውቀዋል፡፡
ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት ወይም የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ማብራሪያና መግለጫ ሳይሰጡ፣ ምስላቸውንና እነሱ እንደተናገሩ በማስመሰል በአንዳንድ ድረ ገጾችና የመገናኛ ብዙኅን እየተገለጸና እየተጻፈ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ሕዝቡ ወደ ትርምስና አላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገባ የሚያደርጉትን አመስግነዋል፡፡ ቤተ ክህነት ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ የምትፈልግና የምትደግፍ መሆኑን አክለው፣ ያልተባለን ተብሏል ብሎ ፎቶን በማስደገፍ ባገኙት ቦታ መለጠፍ የሚያስጠይቅ ከመሆኑም ባሻገር ተገቢ አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡

POSTED BY. DAWIT DEMELASH

No comments:

Post a Comment